በሸገር ከተማ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - አስተዳደሩ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2017(ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።

በከተማው በኩራ ጅዳ ክፍለ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዛሬ ተጀምሯል።

በከተማው በበጀት ዓመቱ ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የተገነቡ የመሰረት ልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።


 

የከተማው ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) በምረቃ ሥነስርዓቱ እንደገለጹት የከተማዋን ልማት በማጠናከር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

በበጀት ዓመቱ በ17 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር 384 ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አስታውሰው፣ ከእነዚህ ውስጥ የ308ቱ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ በቅተዋል ብለዋል።

ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል የመስኖና የመጠጥ ተቋማት፣ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ፣ መንገዶች፣ ፖሊስ ጣቢያ እና የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን በማሳያነት ጠቅሰዋል።


 

የኩራ ጅዳ ክፍለ ከተማ ሀላፊ ጫላ ደሬ በበኩላቸው ለህብረተሰቡ የልማት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ በክፍለ ከተማው ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተከናወኑ 24 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የህዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፣ ህዝቡም ለፕሮጀክቶች ስኬታማነት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

ከልማት ፕሮጀክቶቹ ምረቃ በተጨማሪ የከተማው ነዋሪዎችን ያሰተፈ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በከተማው ኩራ ጅዳ ክፍለ ከተማ ድሬ ሶኮሩ ወረዳ ዛሬ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) እንዳሉት በክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ከ40 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ለምግብነት፣ ለደንና ለውበት የሚውሉ ችግኞች ይተከላሉ።


 

በተመረጡ ክፍለ ከተሞችም የአቮካዶና የአፕል ችግኞችን በመትከል በክልስተር የማልማት ስራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

በችግኝ ተከላው ከተሳተፉ የኩራ ጅዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ በቀለ ያኢ እና አቶ በላቸው አበራ ችግኝ ከመትከል ባለፈ በየጊዜው በመንከባከብ ለማሳደግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ችግኝ መትከል የአየር ንብርት ለውጥን ለመቋቋምና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ በየዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ ልማት እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሀግብር ችግኝ በመትከል አሻራቸውን ማኖራቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸው፣ በቀጣይም የተከሏቸውን ችግኞች በመንከባከብ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም