አዋጁ በውጭ ሀገራት ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች መብታቸውና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዋጁ በውጭ ሀገራት ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች መብታቸውና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አዋጅ በውጭ ሀገራት ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች መብታቸውና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሚያስችል መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 41ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡
አዋጁን አስመልክቶ የተዘጋጀውን የውሳኔ ሀሳብ በምክር ቤቱ የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) አቅርበዋል፡፡
በዚህም አዋጁ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን በተመለከተ ቀደም ሲል ሲሠራባቸው የነበሩት አዋጆች ክፍተቶች የነበሩባቸው በመሆኑና በጊዜ ሂደት አዋጆቹ ያላካተቷቸውን ጉዳዮችን በመለየት ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አዋጅ እንደሆነ ተናግረዋል።
የቀድሞዎቹ አዋጆች የቤት ውስጥ ሠራተኛ፣ የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ ውጭ የትምህርት ዝግጅት የማይጠይቁ የሥራ ዓይነቶችን ባለማካተታቸው ክፍተቶች የተፈጠሩ ስለመሆኑም አንስተዋል።
አዋጁ ሕገ- ወጥ የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪትን ለመከላከልና በውጪ ሀገር ሥራ ስምሪት የዘመነ የአንድ ማዕከል የአሠራር ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል፡፡
በውጭ ሀገራት ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች መብታቸውና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሚያስችል ላኪ ኤጀንሲዎች ተመጣጣኝ የዋስትና ገንዘብ እንዲያስቀምጡ በማድረግ የዜጎችን እንግልት የሚያስቀር አዋጅ በመሆኑ ነው ብለዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አዋጅ ዜጎች ለህገ ወጦች ሳይጋለጡ በአግባቡ ሰልጥነው ተመዝነው እንዲሰማሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በአዋጁ ጠንካራ የሆነ የስልጠናና የምዝና ስርዓት እንደ አንድ ጠንካራ ስርዓት ተደርጎ መካተቱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው፤ አዋጁ ዜጎችን ከህገ ወጥ ደላሎች የሚታደግና የዜጎችን ክብርና ደህንነት የሚያስጠብቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል።