የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ዓለም አቀፍ ትብብር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው

 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2017(ኢዜአ)፦ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ዓለም አቀፍ ትብብር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።

አራተኛው ዓለም አቀፍ የዘላቂ ልማት ፋይናንስ ኮንፍረንስ በስፔን ሲቪያ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በኮንፍረንሱ እየተሳተፈ ነው።

ሚኒስትሩ በኮንፍረንሱ ባደረጉት ንግግር ከ10 አመት በፊት በአዲስ አበባ ሶስተኛው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮንፍረንስ መካሄዱን አስታውሰዋል።

ይሁንና በኮንፍረንሱ የጸደቀው የአዲስ አበባ የድርጊት መርሃ-ግብር የአተገባበር ተግዳሮት እንደገጠመው ጠቅሰው የሲቪያ ስምምነት ይህንን ተግዳሮት የሚሻገር መሆን እንደሚገባው አመልክተዋል።

ዘላቂ የልማት ግቦችን ለመተግበር ከሚያስፈልገው ፋይናንስ ውስጥ የ4 ትሪሊዮን ዶላር እጥረት መግጠሙን አንስተዋል።

ይህ ሁኔታ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራትን ለዘርፈ-ብዙ ተግዳሮቶች ዳርጓቸዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

ለአብነትም አዳጊ ሀገራት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ለሚመጡ ቀውሶች እና ለእዳ ጫና መጋለጣቸው አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች ላይ ፍትሃዊ ዓለም አቀፍ የታክስ ስርዓትን መተግበርና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥላ ስር በየነ-መንግስታዊ የብድር አስተዳደርን በማቋቋም ዘላቂ ያልሆነ የብድር ችግሮችን መፍታት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።

በተጨማሪም የልማት ፋይናንስ ድጋፎችና ብድሮች ሀገራት ቅድሚያ ከሚሰጣቿው ጉዳዮችና እቅዶች ጋር መጣጣም እንዳለባቸውና አዳጊ ሀገራት የሚያገኙት የፋይናንስ ድጋፍ መጨመር እንዳለበት አመልክተዋል።

በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ዘላቂ እና ተገማች የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖራቸውና ቀውሶችን በተገቢው መንገድ ማስተዳደር እንዲችሉና ዓለም ዓቀፍ የልማት ፋይናንስ ስምምነቶች በተገቢው እንዲተገበሩ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባም ነው የገለጹት።

በአፍሪካ እና በአጠቃላይ አዳጊ ሀገራት በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች፣ የስራ ዕድል ፈጠራና የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል የሚያስችል የፋይናንስ አቅርቦት በአስተማማኝ መልኩ ማቅረብ ድህነትን ለመቀነስ እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ሚኒስትሩ ከኮንፍረንሱ ጎን ለጎን “ዓለም አቀፍ ትብብርን በአዲስ መልክ ማደስ” በሚል ርዕስ በሚኒስትሮች ደረጃ በተደረገው ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉ ሲሆን የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ዓለም አቀፍ ትብብር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።

ሁለተኛው ቀኑን የያዘው አራተኛው ዓለም አቀፍ የዘላቂ ልማት ፋይናንስ ኮንፍረንስ እስከ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ልዑክ ከኮንፍረንሱ ጎን ለጎን እየተካሄዱ ባሉ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ላይ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም