በዞኑ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የሕብረተሰቡን ችግሮች እየፈቱ ነው

መቱ ፤ ሰኔ 24/2017 (ኢዜአ)፡-  በኢሉ አባቦር ዞን  የተገነቡ   የተለያዩ  የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች  የሕብረተሰቡን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየፈቱ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ አስታወቁ።

የኦሮሚያ ክልል የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በኢሉአባቦር ዞን አሌ ወረዳ ግንባታቸው የተጠናቀቁ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

የኢሉአባቦር  ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤  በዞኑ   የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በውጤታማነት ተጠናክረው ቀጥለዋል።

ባለፉት ዓመታት በዞኑ የተገነቡ  የመሰረተ ልማት ተቋማት  የሕብረተሰቡን ማህበራዊና  ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመፍታት ተጠቃሚነቱን  በተግባር እያረጋገጡ መሆኑን ገልጸዋል።

እየተገባደደ በሚገኘው በጀት ዓመትም በግንባታ ላይ የቆዩ 656 ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውንም አረጋግጠዋል። 

የአሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ከበደ፣ በወረዳው በ153 ሚሊዮን ብር በጀት የተገነቡ 23 የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች  ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን አስታውቀዋል።


 

ለአገልግሎት ከበቁት ፕሮጀክቶች መካከል የመጠጥ ውሃ ተቋማት፣ ድልድዮችና  የውስጥ ለውስጥ መንገዶች  ይገኙበታል ብለዋል።


 

በምርቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድሳኒ አሚን በበኩላቸው፤  በክልሉ እየተገነቡ  የሚገኙ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ሌሎች የልማት ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር  ማነቃቂያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይ እንደ ድልድይና መንገድ ያሉ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የሕብረተሰቡን ትስስር ከማጠናከር ባሻገር ለኢኮኖሚያዊ ልማት ንቅናቄ ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።


 

ሕብረተሰቡም የተገነቡና በሂደት ላይ  የሚገኙ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶቹን በመጠበቅና በመንከባከብ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአሌ ወረዳ የኦንጋ ቀበሌ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለዘመናት የነበረባቸውን የንጹሕ መጠጥ ውሃ እጥረት ያቃለለላቸው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቀበሌው ነዋሪ አቶ ሁሴን ከበደ ናቸው።


 


 

አቶ ግርማ አባተ እና አቶ ያደታ ዲሳሳ ደግሞ በወረዳው የኦኖኑ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ፤  በአካባቢው የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበረው  ድልድይ   ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም