ባህር ዳር ከተማን ይበልጥ ፅዱና አረንጓዴ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
ባህር ዳር ከተማን ይበልጥ ፅዱና አረንጓዴ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል

ባህርዳር ፤ ሰኔ 24/2017(ኢዜአ)፡- የባህር ዳር ከተማን ይበልጥ ፅዱና አረንጓዴ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በሕብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ ተጠናክረው መቀጠላቸውን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ገለጹ።
"በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ የባህር ዳር ከተማ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ማስጀመረያ የንቅናቄ መረሃ-ግብር ዛሬ ተካሂዷል።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በመርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት ፤ ባህር ዳር ፅዱ ፣አረንጓዴና ደን የተጎናጸፈች ውብ ከተማ ናት።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብሮች የተተከለው ችግኝ የጽድቀት መጠንን በማሳደግ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አውስተዋል።
ከተማዋ በጣና ሀይቅና በዓባይ ወንዝ የተከበበች መሆኗን በመጠቀም በአረንጓዴ ልማት ለኑሮና ለቱሪስት የተመቸች ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ባህር ዳርን ይበልጥ ፅዱና አረንጓዴ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በሕብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ የሰው ዘር ደመላሽ በበኩላቸው፤ በባህር ዳር በክረምቱ ከ492 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቀዋል።
ከተዘጋጀው ችግኝ ውስጥም 45 በመቶ ለምግብነት የሚያገለግል አቡካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ ፓፓያና ሌላም የፍራፍሬ ችግኝ መሆኑን አመላክተዋል።
የችግኝ ተከላውን ለማሳካትም ጉድጓድ መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ ለተከላ ከተለየው መሬት ውስጥም ከ199 ሄክታሩ ካርታ ተሰርቶለታል ብለዋል።
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ሙሉጌታ ዳኛው በሰጡት አስተያየት፤ ችግኝ ለማንም ተብሎ ሳይሆን ለራስና ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ጥቅም ያለው መሆኑን በማመን ዛሬ መትከል መጀመራቸውን ተናግረዋል።
የሚተከለውን ችግኝም ከአካባቢያቸው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ተንከባክበው ለማሳደግ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
የአረንጓዴ ልማት ላይ በራሳቸው ተነሳሽነት እየተሳተፉ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ አበባ ሀይሉ ናቸው።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የግብርና ባለሙያዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች በአዲስ ዓለም ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል።