በሌማት ትሩፋት እየተገኘ ያለው ውጤት እየጨመረ ነው - ግብርና ሚኒስቴር

 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2017(ኢዜአ)፦ በሌማት ትሩፋት መርኃ-ግብር እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት በየአመቱ እየተገኘ ያለው ውጤት እየጨመረ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

የሌማት ትሩፋት መርኃ-ግብር ከተጀመረ 3 አመታት የተቆጠረ ሲሆን በዚህም በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በሀገሪቱ ከዛሬ ሶስት አመት በፊት የተጀመረው የሌማት ትሩፋት በርካታ አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡበት ነው፡፡

በተለይ መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ግዜ ጀምሮ በሀገሪቱ የወተት፣ የዶሮ ሥጋ፣ እንቁላል፣ የማርና ዓሳ ምርት እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በመንግስት የተሰጠው ትኩረት ባሻገር ከፍተኛ የህዝብ ፍላጎት፣ የባለሃብቶች ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ በየአመቱ በዘርፉ የሚገኘው ውጤት እንዲያድግ ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል።


 

በበጀት አመቱ 11 ወራት ብቻ በወተት በእንቁላል በሌሎች የእንስሳትና እንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች ላይ የተገኘው ውጤት ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ እንደታየበት ለአብነት አንስተዋል፡፡

በበጀት አመቱ አስራ አንድ ወራት 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን እንስሳት ማዳቀል፣ 11 ነጥብ 4 ቢሊየን ሊትር ወተት፣ 7 ነጥብ 4 ቢሊዮን እንቁላል ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ህብረተሰቡ ከውሃ አካላትና ከኩሬዎች በተጨማሪ በየአካባቢው፣ በጓሮው፣ በአነስተኛ ቦታ ዓሳ እንዲያመርት ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ እንደሆነም ተናግረዋል።


 

በባህርዳር፣ በባቱ፣ በአርባ ምንጭ፣ በሐዋሳ እና በሰበታ የሚገኙ ዓሳ ጫጩት ማስፈልፈያ ማዕከላትን የማጠናከር ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።


 

ባለፉት ሶስት አመታት በተሰራው ስራ የአሳ ምርት አቅርቦት እያደገ ሲሆን ባለፉት 11 ወራት ብቻ 253ሺህ ቶን የዓሳ፣ 190 ሺህ ቶን የዶሮ ስጋ እንዲሁም 296ሺህ ቶን የማር ምርት መገኘቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም