የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባለፈ የምግብ ዋስትና መሰረት ሆኖ እንዲዘልቅ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባለፈ የምግብ ዋስትና መሰረት ሆኖ እንዲዘልቅ እየተሰራ ነው

አምቦ፤ ሰኔ 24/2017 (ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተፈጥሮ ሃብት ልማት ባለፈ የምግብ ዋስትና መሰረት ሆኖ እንዲዘልቅ እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ ገለጹ።
የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ፤ በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ በመገኘት የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስጀምረዋል።
ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ቀደም ሲል ዝግጅት መደረጉን አንስተው ችግኞች ለተከላ ዝግጁ በመሆናቸው ሁሉም አሻራውን እንዲያኖር አስገንዝበዋል።
በክልሉ ከዚህ በፊት የተተከሉ ችግኞች ለምተው ጥቅም በመስጠት ላይ መሆናቸውን አንስተው በቀጣይም ለደን ልማት፣ ለምግብነት የሚውሉ እና ለውበት የሚያገለግሉ ችግኞች የሚተከሉ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ለዚህ መርሃ ግብር መሳካት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አሻራውን ለማኖር የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲዳ ጉደታ፤ ለችግኝ ተከላው በተመረጡ አካባቢዎች ጎድጓዶች ተቆፍረው ዝግጁ መደረጋቸውን አንስተው ሁላችንም በመትከል አሻራችንን እናኑር ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዞኑ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምግብ ዋስትና እና ለደን ልማት የሚሆኑ ችግኞች መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።