በዩኒቨርሲቲው የተደረገልን አቀባበል በተረጋጋ መንፈስ ለመፈተን አስችሎናል-የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች

ዲላ፣ ሰኔ 24/2017 (ኢዜአ) ፦በዲላ ዩኒቨርሲቲ የተደረገላቸው አቀባበል እና ለፈተናው ያደረጉት ዝግጅት በተረጋጋ መንፈስ ለመፈተን እንዳስቻላቸው በዩኒቨርሲቲው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች ገለጹ።

ተማሪዎች ከሥነ ልቦና ጫና ነጻ ሆነው ፈተናውን በተረጋጋ መንፈስ እንዲወስዱ የተቀናጀ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም የዲላ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል።


 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች መካከል በሻኪሶ ወረዳ የማጋዶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ኤፍራታ ዮሐንስ እንደገለጸችው፣ በዩኒቨርሲቲው የተደረገላቸው አቀባበል እና እያገኙት ያለው የተማሪዎች አገልግሎት ፈተናውን በእርጋታ ለመውሰድ አስችሏታል።

በበይነ መረብ እየተሰጠ ያለው ፈተና ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀምና  ኩረጃን  ለማስቀረት ማስቻሉን የተናገረው ደግሞ ሌላው ተፈታኝ ተማሪ አማኑኤል ሽፍራው ነው።


 

በዩኒቨርሲቲው የተደረገላቸው አቀባበልና ለፈተናው ሲያደርጉት የነበረው ዝግጅት ፈተናውን በተረጋጋ ሁኔታ ለመውሰድ እንዳስቻላቸውም ተናግሯል። 

በዲላ ከተማ አስተዳደር የቆፌ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ትዝታ ግርማ በበኩሏ ፈተናውን ተረጋግተው እንዲሰሩ  ባለድርሻ አካላት እገዛ ማድረጋቸውን ጠቅሳለች።


 

በእዚህም ሀሳባቸውን ፈተናው ላይ ብቻ በማድረግ በተዘጋጁት ልክ ፈተናውን እየወሰዱ መሆኑን ጠቅሳ፣ በፈተናው ስኬታማ ለመሆን የራሷን ዝግጅት ስታደርግ መቆየቷን አስታውሳለች። 

በትምህርት ሚኒስቴር የዲላ ዩኒቨርሲቲ የፈተና ማዕከል ሃላፊ አቶ እስክንድር ላቀው በበኩላቸው እንዳሉት  በዩኒቨርሲቲው ከ7 ሺህ ለሚበልጡ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተናው በበይነ መረብና በወረቀት እየተሰጠ ነው።


 

ተማሪዎች ከሥነ ልቦና ጫና እና ተጽእኖ ነጻ ሆነው ፈተናውን በተረጋጋ መንፈስ እንዲወስዱ የተቀናጀ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

ለተፈታኝ ተማሪዎች ከአቀባበል ጀምሮ የምክርና የተለያዩ አገልግሎቶች በቅርበት እየተሰጠ መሆኑን አንስተው ይህም ተማሪዎች ትኩረታቸው ፈተናው ላይ ብቻ እንዲሆን ማድረጉን ጠቁመዋል።

ፈተናው በዩኒቨርሲቲው ሦስት ግቢዎች እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኤልያስ ዓለሙ (ዶ/ር) ናቸው።


 

ኩረጃን ለማስቀረት ተማሪዎች የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ወደፈተና ቦታ ይዘው እንዳይገቡ መደረጉን ጠቁመው በዩኒቨርሲቲው በኩል ለተፈታኝ ተማሪዎች የማደሪያ፣ የምግብና ሌሎች አገልግሎቶችን በማቅረብ ተረጋግተው እንዲፈተኑ መደረጉን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም