ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ ተጨማሪ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት እናደርጋለን - ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ

 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2017(ኢዜአ)፦ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ተጨማሪ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ፈሰስ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ ሥራ ከጀመረ አራት ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፤ በዚሁ ጊዜ አስር ሚሊዮን ደንበኞችን አፍርቷል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዊም ቫንሄለፑት ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ መንግስት የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች መክፈቱን ተከትሎ ሳፋሪኮም ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን አስታውሰዋል።

በዚህም የቴሌኮም ዘርፉን ፈጣንና ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል ሙዓለንዋይ ማፍሰሱን ጠቅሰው፥ ባለፉት ዓመታት በቴሌኮምና ዲጂታል ፋይናንስ ላይ በስፋት መስራቱንም አንስተዋል።


 

በአሁኑ ወቅት ከ150 በላይ የኢትዮጵያ ከተሞች ከሦስት ሺህ በላይ የኔትወርክ ማማዎችን መገንባቱንና ፈጣን የአራተኛ ትውልድ ኔትወርክን ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አብራርተዋል።

የሳፋሪኮም አገልግሎትን በንቃት የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር አስር ሚሊዮን መድረሱ ትልቅ ስኬት መሆኑንም ጨምረው አስታውቀዋል።

ባለፋት አራት ዓመታት የቴሌኮም አገልግሎቱን ለማስፋት 300 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ፈሰስ ማድረጉንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ባለሃብቶች መክፈቷን አድንቀው፥ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በቀጣይም ኢንቨስት ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ኃላፊ አንዷለም አድማሴ(ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች መክፈቱ በርካታ ዕድሎችን ይዞ እንደመጣ አስታውቀዋል።

ፈጠራና ኢኖቬሽንን የበለጠ በማሳደግ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ጥረትን ለማገዝ ሳፋሪኮም ቁርጠኛ መሆኑን አመልክተዋል።


 

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽነቱን በማስፋት መሰረተ ልማትን ለማስፋትና የደንበኞቹን ፍላጎት ለማሟላት አንደሚሰራ ተናግረዋል።

በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት አገልግሎቶችን ለማስፋት ተጨማሪ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚያደርግና ተደራሽነቱንም በእጥፍ እንደሚጨምር አመልክተዋል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠሩን አመልክተው፥ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የደንበኞቹን ቁጥር ከሃምሳ እስከ ሰባ ሚሊዮን ለማድረስ እንደሚሰራም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም