በክልሉ ግንባታቸው የተጓተቱ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ግንባታቸው የተጓተቱ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተደረገ ነው

ቦንጋ፤ ሰኔ 24/2017 (ኢዜአ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግንባታቸው የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።
ምክትል ርዕሰ መሰተዳድሩ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባውን የአውራዳ ኢንዱስትሪያልና ኮንስትራክሽን ኮሌጅን ዛሬ መርቀዋል።
ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር) እንደገለጹት በክልሉ ግንባታቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንጻር ጉልህ ሚና ቢኖራቸውም በተለያዩ ምክንያቶች ተጓትተው ቆይተዋል።
በአሁኑ ወቅትም የተጓተቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለይቶ ግንባታቸውን በማፋጠን ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ክልሉ ራሱን ችሎ ከመቋቋሙ በፊት ተጀምረው የነበሩ 10 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን ለማጠናቀቅ በተሰራው ሥራ በዚህ ዓመት ሦስቱን ማጠናቀቅ እንደተቻለ ጠቅሰው፣ ቀሪዎችን በቀጣይ ዓመት የማጠናቀቅ ሥራ ይሰራል ብለዋል።
በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በክህሎት የበቁ ሥራ ፈጣሪ ዜጎችን ከማፍራት ባለፈ ተኪ ምርት ለማምረት የሚያደርጉትን ጥረት ለማጠናከር እንደሚሰራም ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር) አመልክተዋል።
ለኮሌጁ ግንባታ ከ53 ሚሊዮን 800 ሺህ ብር በላይ ወጪ መደረጉን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አብይ አንደሞ (ዶ/ር) ናቸው።
ኮሌጁ በውስጡ ለመማሪያ ክፍል፣ ለቤተመጻህፍት፣ ለመሰብሰቢያ አዳራሽና ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ባለሁለት ወለል ህንጻዎችን አካቶ የተገነባ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዜጎች ከሥራ ጠባቂነት ተላቀው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ሙያና ክህሎት የሚጨብጡበት መሆኑንም አመልክተዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንደሻው ከበደ በበኩላቸው፣ ዛሬ ለምረቃ የበቃው ፕሮጀክት በክልሉ የዘገዩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አንድ ማሳያ ነው" ብለዋል።
በኮሌጁ ያልተሟሉ ግብዓቶችን ለማሟላት በተቀናጀ መንገድ እንደሚሰራ ተናግረው፣ ኮሌጁ ብቃት ያላቸውን ዜጎች አሰልጥኖ ለማውጣት በሚያደርገው ጥረት ዞኑ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኮሌጁ መመረቅ የአካባቢውን ህብረተሰብ የቆየ የልማት ጥያቄ መልሷል ያሉት ደግሞ የአውራዳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ታረቀኝ ሀይሌ ናቸው።
ኮሌጁ የበለጠ እየተጠናከረ እንዲመጣ በወረዳው በኩል ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው እንዲሁም የክልሉ ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ በላይ ተሰማን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገንተዋል።
አመራሮቹ በኮሌጁ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።