ትውልዱ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ለሀገር በጎ አሻራውን ሊያኖር ይገባል - ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2017(ኢዜአ)፦ ትውልዱ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ለሀገር በጎ አሻራውን ሊያኖር ይገባል ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ-ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ-ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ፣ የቤተክርስቲያኗ አባቶች እና የከተማዋ አመራሮች ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።


 

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገርና በከተማ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመከላከል ለዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማይተካ ሚና እየተጫወተ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንም ከጥንት ጀምሮ በገዳማትና አድባራት ችግኞችን በመትከል ለመጠለያነት፣ ለደከማቸው ማረፊያና ለትውልድ ማስተማሪያነት እየተጠቀመች ነው ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኞችን በመትከል የመንከባከብ ስራ ከቤተክርስቲያኗ ገዳማትና አድባራት ታሪክ ጋር ጥብቅ ትስስር ያለወ በጎ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለተሻለ ሀገር ግንባታ ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ትውልዱ ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ በጎ ተግባርን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስና ከቤተ-ክርስቲያኗ አባቶች ጋር የአረንጓዴ አሻራችንን አሳርፈናል ብለዋል።

አረንጓዴ አሻራ የሁሉም ዜጋ የጋራ የልማት አጀንዳ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፥ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በመርሃ ግብሩ ችግኝ የመትከል ስራውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።


 

የአዲስ አበባ የውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው በመዲናዋ 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ችግኞችን መትከል የሚያስችል መርሃ ግብር በይፋ መጀመሩን አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና ብጹዓን አባቶች ያካሄዱት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም ለትውልዱ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በቤተ-ክርስቲያኗ የፕሮጀክት መምሪያ ኃላፊ መላዕከ ህይወት ቆሞስ አባ ወልደየሱስ ሰይፉም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ደህንነትን የመጠበቅ እና የበረከት ሥራ ነው ብለዋል።

ቤተክርስቲያኗም በመርሃ ግብሩ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ አርዓያነቷን እንደምታስቀጥል ጠቁመዋል።


 

የቅኔና የመጽሐፍት ትርጓሜ መምህር ሊቀ-ጉባኤያት አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ በበኩላቸው ችግኞችን መትከልና ተንከባክቦ ለፍሬ ማብቃት ከሁላችንም ይጠበቃል ነው ያሉት።

ብፁዓን አባቶች በስፍራው ተገኝተው ያካሄዱት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሁሉም ዜጋ አርዓያ በመሆን ቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ሀገር እንዲረከብ ለማድረግ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮውን 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች የመትከል ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት አካባቢ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም