የኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞና የአዲስ አበባ ለውጥ ለአፍሪካውያን ትልቅ ትምህርት ነው-ዋና ዳይሬክተር ጆርጅ ኦምባዶ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 24/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞና የአዲስ አበባ ለውጥ አፍሪካውያን ህልሞቻቸውን ማሳካት እንደሚችሉ ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነው ሲሉ የአፍሪካ የትብብር፣ቁጠባና ብድር ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ጆርጅ ኦምባዶ ገለጹ፡፡

መንግስት የአዲስ አበባን የአፍሪካ መዲናነት የሚመጥን እና የነዋሪዎችን ህይወት የሚቀይር አስደናቂ የኮሪደር ልማት በማከናወን ላይ መሆኑን ተመልክቻለሁ ብለዋል።


 

ኢዜአ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በተመለከተ ከአፍሪካ የትብብር፣ ቁጠባና ብድር ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ጆርጅ ኦምባዶ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ዋና ዳይሬክተር ጆርጅ ኦምባዶ በአህጉሪቱ የተለያዩ ቦታዎች መዘዋወራቸውን በማውሳት፥ እንደ አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ የሚያስደንቅ ለውጥ ያስመዘገበ ከተማ ግን አላየሁም ብለዋል፡፡

"አዲስ አበባን ከአስር ዓመት በፊት አውቃታለሁ፤ የዚያን ጊዜ የነበራት ገፅታ እና አሁን ያለችበት ደረጃ ልዩነቱ የቀንና የማታ ያክል ነው" ሲሉም ነው በአድናቆት የተናገሩት።

በተለይ የኮሪደር ልማት የተከናወነባቸው የከተማዋ አካባቢዎች ከአንዳንድ ያደጉ ሀገራት ከተሞች የተሻለ ውብ ገፅታ መላበሳቸውን እንደተመለከቱም ጠቅሰዋል።


 

በከተማዋ የተከናወኑ እና እየተከናወኑ ያሉ ሁሉን-አቀፍ የልማት ስራዎች ለአፍሪካውያን የመበልፀግና የመለወጥ ህልማቸውን ለማሳካት ትልቅ ትምህርት እንደሚሆኑም ከጉብኝታቸው መረዳታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እየተሰሩ ያሉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች፣የመስህብ ስፍራዎች ሀገሪቱን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል እና የኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጋት እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡

በአፍሪካ ለሁለንተናዊ እድገት የሚበጅ ትልቅ አቅም መኖሩን ገልጸው፥ አህጉራዊ እምቅ አቅምን በማልማት ማደግና መለወጥ እንደሚቻል ደግሞ የኢትዮጵያ ፈጣን የዕድገት ጉዞ ምሳሌ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም