የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የከተማዋን ገፅታ ቀይሯል - የአዳማ ከተማ ከንቲባ - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የከተማዋን ገፅታ ቀይሯል - የአዳማ ከተማ ከንቲባ

አዳማ/ጅማ ፤ሰኔ 24/2017 (ኢዜአ)፡-የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የከተማዋን ገፅታ መቀየሩን የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ገለጹ።
በከተማዋ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሄዷል።
የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሀይሉ ጀልዴ እንዳሉት የተፈጥሮ ሃብት መመናመንን ለመከላከል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በከተማ አስተዳደሩ የተተከሉ ችግኞች የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ የገቢ ምንጭ በመሆን ጥቅም እያሰገኙ ነው ብለዋል።
በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም በ14 ተፋሰሶች ላይ 120 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ስፍራን ለማልማት ታቅዶ ዛሬ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱን ገልጸዋል።
ከዚህም ባሻገር በትምህርትና በጤና ተቋማት እንዲሁም በወል መሬትና የኮሪደር ልማት በሚካሄድባቸውና በሌሎችም ስፍራዎች የችግኝ ተከላው በስፋት እንደሚካሄድ አውስተዋል።
የአዳማ ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለሙ ቂልጡ በበኩላቸው በከተማዋ ለፍራፍሬና ለዛፍ የሚውሉ ችግኞች እንደሚተከሉ ተናግረዋል።
ለችግኝ ተከላው የቦታ መረጣና ጉድጓድ ዝግጅት ከማድረግ ባለፈ ህብረተሰቡ በበጎ ፈቃድ ለማሳተፍ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በአዳማ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ላይ ችግኝ ሲተክሉ ያገኘናቸው አባገዳ መግራ ለገሰ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በረሃማነትን ለመከላከል አረንጓዴ አሻራ ጉልህ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
የተራቆተ አካባቢን አረንጓዴ ለማልበስ የችግኝ ተከላው ወሳኝ በመሆኑ ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የአዳማ ነዋሪ አቶ ግርማ ቶሌራ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአካባቢያችንን ገጽታ ከመመለስ ባለፈ ለከተማዋ ውበት አሻራ የሚጥል ነው ብለዋል።
በተመሳሳይም የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር በዛሬው ዕለት በከተማዋ የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን አስጀምረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመቀበል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለተከታታይ ስድስት አመታት ችግኝ መተከሉን ጠቁመዋል።
በክረምት ችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ በ12 የችግኝ ጣቢያዎች ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎችና እና ለዛፍ ጥላ የሚያገለግሉ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በጅማ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ከተሳተፉት መካከል አቶ ነጂብ አለሙ በየዓመቱ በሚደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር መሳተፋቸውን ተናግረው መትከል ብቻም ሳይሆን መንከባከብ እንደሚገባም አመልክተዋል።