የወጣቶች ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ መስተጋብርን በማጎልበት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን እያጠናከረ ይገኛል - ሰላም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የወጣቶች ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ መስተጋብርን በማጎልበት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን እያጠናከረ ይገኛል - ሰላም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ሰኔ 24/2017 (ኢዜአ)፦የወጣቶች ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊ መስተጋብር በማጎልበት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝ የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።
በሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ ገመቺሳ ኢቲቻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በእርስ መልካም ግንኙነት ከማጠናከሩ ባሻገር በርካታ ፋይዳ ያለው ተግባር ነው፡፡
ባለፉት አመታት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በየአመቱ በርካታ ወጣቶች መሳተፋቸውን በዚህም ማህበራዊ ግንኙነት ለማስፋትና የማህበረሰብ ቁርኝት ለማዳበር አስተዋጽኦ እንደነበረው ተናግረዋል።
መንግስት ለተለያዩ የልማት ስራዎች የሚያወጣውን ከፍተኛ ወጪ በማስቀረት በኩልም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶች ሀገራዊ መግባባት መፍጠርና ዘላቂ የሰላም ግንባታን ማጠናከር ላይ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችል ተግባራት እየተከናወበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህ ክረምትም የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃድ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን አንስተው፤ አምስት ሺህ የሚሆኑ የበጎ ፈቃደኞች በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል ተሰማርተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
እነዚህ በጎ ፍቃደኞችም በቀጣይ በርካታ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባላቸው ተግባራት ላይ እንደሚሰማሩ አስታውቀዋል፡፡
በዚህም በሚሊየን የሚቆጠሩ ማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን መሪ ስራ አስፈፃሚው ገመቺሳ ተናግረዋል፡፡
በጎ ፍቃደኛ ወጣቶቹ የገጠሩን ማህበረሰብ በእርሻ ስራ፤አቅመ ደካሞችን ማሳ በማገዝ ስራዎች ላይ በልዩ ሁኔታ እንዲደግፉ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡
እንዲሁም ጽዱ አካባቢን ከመፍጠር፣ በአረንጓዴ አሻራ ህብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ የማስተባበበር እንዲሁም በክረምት ትምህርት ስራዎችን ጨምሮ ወደ አስራ አራት በሚደርሱ ተግባራት ላይ እንደሚሰማሩ ገልጸዋል።
እንደ መሪ ስራ አስፈፃሚ ገመቺሳ ኢቲቻ ገለጻ የወጣቶች ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊ መስተጋብር በማጎልበት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ ይገኛል።