የአውሮፓ ስመ ገናናዎቹ  ሪያል ማድሪድ እና ጁቬንቱስ ጨዋታ ተጠባቂ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2017 (ኢዜአ)፦  በፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር የመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሀርድ ሮክ ስታዲየም ሪያል ማድሪድ ከጁቬንቱስ የሚያደርጉት ጨዋታ የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያን ቀልባቸውን ጥለውበታል።

የአምስት ጊዜ የፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ አሸናፊው ሪያል ማድሪድ በምድብ ስምንት በሰባት ነጥብ የምድቡ መሪ በመሆን ማጠናቀቁ ይታወቃል።

በውድድሩ የመጀመሪያ ተሳትፎውን እያደረገ የሚገኘው ጁቬንቱስ በምድብ ሰባት ስድስት ነጥብ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብቷል። 

የአውሮፓ ኃያላኑ ሪያል ማድሪድ እና ጁቬንቱስ በሁሉም ውድድሮች እስከ አሁን 21 ጊዜ ተገናኝተዋል።


 

ሪያል ማድሪድ 10 ጊዜ በማግኘት ውስን ብልጫ ወስዷል። ጁቬንቱስ 9 ጊዜ ሲያሸንፍ 2 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። 

በ21ዱ ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድ 26 ግቦችን ሲያስቆጥር ጁቬንቱስ 25 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። 

ሁለቱ ክለቦች ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ2017 በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ነበር። በካርዲፍ በተካሄደው ጨዋታው ሪያል ማድሪድ 4 ለ 1 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስቷል።

በአውሮፓ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ትልቁ የክለቦች ባላንጣነት ማሳያ ተደርጎ የሚጠቀሰው የቡድኖቹ ፍልሚያ ሁሌም ጠንካራ እና እልህ አስጨራሽ ፉክክር የሚደረግበት ነው።

ሪያል ማድሪድ እና ጁቬንቱስ የየሊጋቸውን ዋንጫ በተመሳሳይ 36 ጊዜ በማንሳት የበላይነቱን ይዘዋል። 

በአውሮፓ መድረክ ሪያል ማድሪድ 15 ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ ከፍ በማድረግ ስኬታማ መሆን የቻለ ክለብ ነው። ጁቬንቱስ ሁለት ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አንስቷል። 

የእግር ኳስ ባለሙያዎች ከወቅታዊ ብቃት አንጻር ሪያል ማድሪድ ጁቬንቱስን በጠባብ የግብ ልዩነት ሊያሸንፍ ይችላል የሚል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

በጥሎ ማለፍ የመጨረሻ መርሃ ግብር ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከሞንቴሬይ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ በሜርሴዲስ ቤንዝ ስታዲየም ይጫወታሉ።


 

ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በሰባት ነጥብ የምድብ ስድስት መሪ፣ ሞንቴሬይ በምድብ አምስት በአምስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ጥሎ ማለፍ ገብተዋል።

ሁለቱ ክለቦች እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። 

የሁለቱ ጨዋታ አሸናፊዎች በሩብ ፍጻሜው ይገናኛሉ።

በአሜሪካ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ ፒኤስጂ፣ ባየር ሙኒክ፣ ቼልሲ፣ ፓልሜራስ፣ አል ሂላል እና ፍሉሜኔንሴ እስከ አሁን ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉ ክለቦች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም