ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በዲጂታል ስርዓቱ ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል-ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2017 (ኢዜአ)፦ባለፉት አምስት አመታት ሲተገበር የቆየው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በዲጂታል ስርዓቱ ውጤት አስገኝቷል ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት የአንድን ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ማረጋገጥ የሚቻለው የአሰራር ስርዓትን በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በኢኖቬሽን ሲደገፍ ነው። 

ኢትዮጵያም ወደ ዲጂታል ስርዓት መግባት የሚያስችላትን የህግ ማዕቀፍ እንዲሁም ስትራቴጂ በማዘጋጀት ወደ ስራ እንደገባች  ገልጸዋል።

በተጨማሪም ወደ ዲጂታል ስርዓቱ መግባት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች ተሟልተው ተግባራዊ መደረግ መጀመራቸውን አስታውቀዋል። 

ስትራቴጂው ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያና የ10 አመት መሪ የልማት ዕቅድ ስትራቴጂዎች እንዲሁም ከአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ጋር ተሳስሮ ሲተገበር መቆየቱንም ገልጸዋል።

ባለፉት አመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ  ከአንድ ወር በኋላ እንደሚጠናቀቅ ገልፀው በቀጣይ 2030 ድረስ ተግባራዊ የሚደረገው የ5 አመት ስትራቴጂ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ነው የጠቀሱት።

ባለፉት አምስት አመታት ሲተገበር የቆየው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፉ ላይ አመርቂ ውጤቶች እንደተመዘገቡቡት  ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ባለፉት አምስት አመታት የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት በመዘርጋት፣ የዲጂታል አገልግሎት በማስፋት እንዲሁም የዲጂታል መታወቂያ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸው አንስተዋል። 

የመንግስትን የአሰራር ስርዓት ከማዘመን ጋር በተያያዘ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን እውን ለማድረግ ከተሰሩ ስኬታማ ስራዎች መካከል መሆኑን ገልፀዋል።

ማዕከሉ በአንድ ጣራ ስር የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችን በማጣመር  አገልግሎት እየሰጠ  እንደሚገኝ  አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይም  የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወደ ክልል ከተሞች በማስፋት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም