በክልሉ በዲጅታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ በተቋማት የአገልግሎት አሰጣጡን የማሻሻል ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በዲጅታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ በተቋማት የአገልግሎት አሰጣጡን የማሻሻል ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው

ሀዋሳ ፤ሰኔ 24/2017 (ኢዜአ) ፡-በዲጅታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ በእውቀትና ክህሎት የዳበሩ ባለሙያዎችን በማፍራት በተቋማት የአገልግሎት አሰጣጡን የማሻሻል ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የሲዳማ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የሲዳማ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ በክልሉ ለዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስን የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አሰፋ ጉራቻ፤ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና የተገልጋዮችን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን አንስተው ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በተደረገ የዳሰሳ ጥናት የተገልጋዮች እርካታ ከ47 በመቶ ወደ 66 ነጥብ 3 በመቶ ከፍ ማለቱ ተመላክቷል።
ለመሻሻሉ ምክንያት የማዘጋጃ ቤቶች፣ ትራንስፖርት፣ የገቢዎችን ጨምሮ 7 የተለያዩ ሴክተሮችን የአገልግሎት ክፍተቶች በመለየት በቴክኖሎጂ ጭምር የታገዘ አሰራር በመዘርጋት መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይም አገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ለማጠናከር በድጅታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በመዘርጋት በእውቀትና በክህሎት የዳበረ አገልጋይ የመፍጠር ትኩረት ይደረጋል ሲሉ አረጋግጠዋል።
ለተመደቡበት የሥራ ዘርፍ ቃላቸውን ጠብቀውና ሃላፊነት ወስደው የማገልገል ችግር ያለባቸው አመራርና ሰራተኞች ሲያጋጥሙ በአሰራሩ መሰረት እርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ ታደለች ዮሐንስ፤ በቢሮው እየተደረጉ ያሉ የአሰራር ማሻሻያዎች እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ስራዎች ለውጥ ማምጣታቸውን አንስተዋል።
በዚህም የአገልጋዮች አቅም እየዳበረ የተገልጋዮች እርካታም እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።፡
በሥልጠናው ከ240 በላይ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡