አል ሂላል ማንችስተር ሲቲን በማሸነፍ ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደ ሩብ ፍጻሜ ገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
አል ሂላል ማንችስተር ሲቲን በማሸነፍ ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደ ሩብ ፍጻሜ ገብቷል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2017 (ኢዜአ)፦ በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ማለፍ መርሃ ግብር አል ሂላል ማንችስተር ሲቲን 4 ለ 3 አሸንፏል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በካምፒንግ ወርልድ ስታዲየም ተካሄዷል።
ትናንት ከእኩለ ሌሊት በኋላ ጀምሮ እስከ ዛሬ ማለዳ በዘለቀው ጨዋታ በርናንዶ ሲልቫ በዘጠነኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል ሲቲን መሪ አድርጓል።
ማርኮስ ሊኦኖርዶ በ46ኛው እና ማልኮም በ56ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ባሳረፏቸው ግቦች አል ሂላልን መሪ ሆኗል።
ኤርሊንግ ሃላንድ በ55ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ቡዱኑን አቻ አድርጓል።
ቡድኖቹ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለት አቻ በመለያየታቸው ወደ ተጨማሪ 30 ደቂቃ አምርተዋል።
በተጨማሪ ሰዓት ካሊዶ ኩሊባሊ በ94ኛው ደቂቃ አል ሂላልን መልሶ መሪ ቢያደርግም ፊል ፎደን በ104ኛው ደቂቃ ማንችስተር ሲቲን በድጋሚ አቻ እንዲሆን አስችሏል።
ማርኮስ ሊኦናርዶ በ112ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ጎል አል ሂላልን ወደ ሩብ ፍጻሜ ልኳል።
ልብ አንጠልጣይ ፋክክር በተደረገበት ጨዋታ የአል ሂላል የአልሸነፍ ባይነት ጽናት ባለድል አድርጓታል።
ሁለት ግቦቹን ያስቆጠረው ማርኮስ ሊኦናርዶ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
የአል ሂላል ግብ ጠባቂ ያሲን ቦኖ 10 ኳሶችን በማዳን ቡድኑን በጨዋታው እንዲቆይ በማድረግ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
የሳዑዲ አረቢያው ቡድን የአውሮፓውን ክለብ በማሸነፍ ዓለም ያልጠበቀውን ውጤት አስመዝገቧል።
አል ሂላል በሩብ ፍጻሜው ከፍሉሜኔንሴ ጋር የፊታችን አርብ ይጫወታል።
ፍሉሜኔንሴ ትናንት ኢንተር ሚላንን 2 ለ 0 አሸንፏል።