ኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ግንኙነቷን ለማጠናከር እና የስትራቴጂክ አጋርነቷን ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦   ኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ግንኙነቷን ለማጠናከር እና የስትራቴጂክ አጋርነቷን አድማስ የበለጠ ማስፋት በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አስታወቀች።

10ኛው የእስያ የመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ባንክ  (AIIB) ዓመታዊ ስብስባ በቻይና ቤጂንግ ተካሄዷል።

በስብስባው ላይ የገንዘብ ሚኒስትር እና የ2024/25 የባንኩ አስተዳደሪዎች ቦርድ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አሕመድ ሽዴ ተሳትፈዋል።

ሚኒስትሩ ከስብስባው ጎን ለጎን ከፋይናንስ ተቋማት እና የልማር አጋሮች ጋር የተለያዩ የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርገዋል።

ከተሰናባቹ የእስያ የመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ባንክ  ጂን ሊኪን ጋር በነበራቸው ቆይታ ጂን የ10 ዓመት የአገልግሎት ቆይታቸው ባንኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ክብር የሚሰጠው ተቋም እንዲሆን ያከናወኑትን ስራ አድንቀዋል። 

በውይይቱ ባንኩ ትራንስፖርት፣ ኢነርጂ እና የማዘጋጃ ቤታዊ መሰረተ ልማት ጨምሮ በኢትዮጵያ ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ከቻይና የፋይናንስ ሚኒስትር እና የእስያ የመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ባንክ የገዢዎች ቦርድ ሰብሳቢ ላን ፎአን፣ ከኳታር የፋይናንስ ሚኒስትር አሊ አል ኩዋሪ ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ ከቻይና ልማት ባንክ፣ ለቻይና የኤክስፖርት እና ኢምፖርት ባንክ እና ከይና ኢንዱስትሪና ንግድ ባንክ አመራሮች ጋርም ተነጋግረዋል።

ውይይቶቹ በልማት ፋይናንስ፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማፋጠን እና የኢትዮጵያን የእድገትና የማይበገር አቅም መገንባት አጀንዳ የኢኖሼሽን አማራጮችን ተጠቅሞ መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የባለብዙ ወገን ግንኙነቷን ለማጠናከር፣ የአረንጓዴና ሁሉን አቀፍ እድገትን ለማሳለጥ እንዲሁም ለኢትዮጵያውያን እና አፍሪካ ውጤቶችን የሚያስገገኙ ስትራቴጂካዊ አጋርነቶችን ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጻለች።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የ10 ዓመት የልማት እቅዷ እና ለሰፊው ቀጣናዊ ትስስር አጀንዳዋ ድጋፍ እንዲያገኝ ከእስያ የመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ባንክ እና ሌሎች ተቋማት  ጋር በትብብር እንደምትሰራ የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም