አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ያላትን የጸና ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው- ሚኒስትር አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ያላትን የጸና ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው- ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦ አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እና ከባቢ አየርን ለመጠበቅ ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።
10ኛው የእስያ የመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ባንክ (AIIB) ዓመታዊ ስብሰባ በቻይና ቤጂንግ ተካሄዷል።
በስብሰባው ላይ የገንዘብ ሚኒስትር እና የ2024/25 የባንኩ አስተዳደሪዎች ቦርድ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አሕመድ ሽዴ ተሳትፈዋል።
የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ፣ የባንኩ ዓለም አቀፍ አባል ሀገራት እና ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በስብሰባው ላይ ተሳትፎ አድርገዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር እና የ2024/25 የባንኩ ገዢዎች ቦርድ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አሕመድ ሽዴ በስብሰባው ላይ የኢትዮጵያ ሪፎርም እና የልማት ግቦችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የላቀ አመራር ሰጪነት ለውጥ እያስመዘገበች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ለውጡ የተገኘው በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ እንደሆነና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠር፣ የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ፣ የአስተዳደር አቅምን ለማሻሻል እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የማይበገር እና ከወቅቱ ጋር የሚራመድ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና ከባቢ አየርን ለመጠበቅ ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው ብለዋል።
የኢኮኖሚ ሪፎርሙ እና የአረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ፈተናዎች ሁሉን አቀፍ፣ ጊዜው የደረሰባቸው የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል አማራጮች እና ሀገር በቀል መፍትሄዎችን ለማበጀት ያላትን የአመራር ቁርጠኝነት አንስተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር እና የ2024/25 የባንኩ አስተዳዳሪዎች ቦርድ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አሕመድ ሽዴ የእስያ የመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ባንክ ገዢዎች የንግድ የጠረጴዛ ዙሪያ ምክክር በአወያይነት መርተዋል።
ውይይቱ በዘላቂ ትስስር እና መሰረተ ልማት ላይ ያተኮረ ነው።
#Ethiopian_News_Agency
#ኢዜአ
#Ethiopia
#ኢትዮጵያ