የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት የ50 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ያደርጋል-የባንኩ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና

አዲስ አበባ ፤ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ልማት ባንክ የሌማት ትሩፋት አካል ለሆነው የኢትዮጵያ የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት የ50 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን የባንኩ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና ገለጹ።

ዓለም አቀፍ የዘላቂ ልማት ፋይናንስ ኮንፍረንስ ዛሬ በስፔን ሲቪያ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የተመራ ልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን ወክሎ በኮንፍረንሱ ላይ እየተሳተፈ ነው።

“Global Alliance Against Poverty and Hunger” ከኮንፍረንሱ ጎን ለጎን ያዘጋጀው ስብሰባ ተካሄዷል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በሌማት ትሩፋት ዙሪያ ያላት ልምድ እንደ ተምሳሌታዊ ፕሮጀክት በስብሰባው ላይ አቅርበዋል።

በተጨማሪ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምታደርጋቸውን ሌሎች ሰፋፊ ጥረቶች አስመልክቶ ያላትን ተሞክሮም አጋርተዋል።

ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ድህነትን ለመቀነስ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

ኢኒሼቲቩ ድህነትን ለመቀነስ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሀገር በቀል ሀሳቦችን እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል።

በመንግስት እና በህዝቡ በባለቤትነት የተያዘ መሆኑ፣ድህነትን በመቀነስ እና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንጻር ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢኒሼቲቭ በሀገር ውስጥ ሀብት ላይ በመመስረት የሚተገበር መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ለምታደርጋቸው ትብብሮች ለኢኒሼቲቩ ድጋፍ በማፈላለግ ድህነትን ለመቀነስ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ሊኖረው ይችላል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

አክለውም ኢኒሼቲቩን በተጨማሪ ኢንቨስትመንት በስፋት መተግበር እንደሚቻል ገልጸው፥ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ የተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎረም ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አመልክተዋል።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሌሎች ሀገራት መልካም ተሞክሮ ለመማርም ዝግጁ ናት ብለዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በሰራችው አመርቂ ስራ በስንዴ ምርት ሙሉ በሙሉ ራሷን መቻሏን ገልጸዋል።

በትኩረት ተገቢው አመራር እና ድጋፍ ከተደረገ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚቻል የኢትዮጵያ ስኬት እንደ ተጨባጭ ማሳያ ሊወሰድ እንደሚችል አመልክተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ባንኩ የኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋት አካል የሆነውን የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት 50 የሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለመደገፍ መወሰኑን ይፋ አድርገዋል።

ኮንፍረንሱ እስከ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከኮንፍረንሱ ጎን ለጎን በሚኖሩ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ላይ ተሳትፎ ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም