በፍትሐ ብሄር ክርክር ወቅት የተቋማት አመራሮች አስፈላጊ መረጃዎችን አደራጅቶ የማቅረብ ልምድና በቂ ግንዛቤ ሊያዳብሩ ይገባል

ባህርዳር ፤ሰኔ 23/2017 (ኢዜአ) ፡-በፍትሐ ብሄር ክርክር ወቅት የተቋማት አመራሮች አስፈላጊ መረጃዎችን አደራጅቶ የማቅረብ ልምድና በቂ ግንዛቤ ሊያዳብሩ እንደሚገባ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

መንግስት ተከራካሪ በሆነባቸው የፍትሃ ብሄር ጉዳዮች በሚያጋጥሙ ችግሮችና መፍትሄዎች፤ የክልሉ ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅና የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት  ጋር የውይይት መድረክ በባህር ዳር እየተካሄደ ይገኛል። 

የመድረኩ ዓላማ የመንግስት ተቋማት የፍትሃ ብሄር ክርክር ሲያጋጥማቸው በጉዳዩ ላይ የተሟላ ዝግጅት በማድረግና አስፈላጊ መረጃዎችን ለፍርድ ቤቶች በማቅረብ የህዝብና የመንግስት ንብረቶችን ለመጠበቅ መሆኑም ታውቋል። 

በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አለምአንተ አግደው፤ የመንግሥት ተቋማት የፍትሃ ብሄር ክርክር ሲያጋጥማቸው የሚስተዋሉ ክፍተቶች እየተበራከቱ መሆኑን አንስተዋል። 

የፍርድ ቤቶች ሚና ነፃ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በክርክር ሂደት ከሚዛናቸው በመጉደል በተቋማት አሰራሮች የሚታዩ ክፍተቶችን ሊሸፍኑ የማይችሉ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህ ረገድ በየደረጃው ያሉ የመንግስት ተቋማት አመራሮች ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ገልጸው ይህ ሲባል ግን ፍርድ ቤቶች የመንግሥትና የሕዝብ ጥቅም በሚጎዳበት አጋጣሚ በዝምታ ይመለከታሉ ማለት አይደለም ብለዋል። 

በመሆኑም የመንግሥት ተቋማት የተቋሞቻቸውን ጉዳዮች በአግባቡ መምራትና የፍትሐ ብሔር ክርክር ሲያጋጥም አስፈላጊ ማስረጃዎችን በማቅረብ የህዝብን ሃብትና ንብረት መጠበቅና ማስከበር እንዳለባቸው አንስተዋል። 

የክልሉ መሬት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሰይፉ የሱፍ፤ በመንግስት የተያዙ የፍትሃ ብሄር ክሶች በአግባቡ ክርክር ስለማይደረግባቸው ከፍተኛ ሃብት እየታጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በፍርድ ቤቶች ከሚካሄዱ ክርክሮች በአብዛኛው መሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች መሆናቸውን አንስተው ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ህግ አውጭውና ህግ ተርጓሚው ከአስፈፃሚው ጋር ተቀራርቦ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በምክክር መድረኩ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም