ግብርናውን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ አማራጭ የኤክስቴንሽን አገልግሎቶችን ማስፋት ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
ግብርናውን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ አማራጭ የኤክስቴንሽን አገልግሎቶችን ማስፋት ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦በምግብ ራስን ለመቻል የተያዘውን ግብ ለማሳካትና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አማራጭ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎቶችን ማስፋት እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ።
ቋሚ ኮሚቴው የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለግብርና ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።
የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ተደራሽነት ለማስፋት፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በመድረኩ ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላትና ከሕግ ባለሙያዎች ለተነሱ ጥያቄዎች የግብርና ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚሁ ወቅት የግብርና ዘርፉ የአገሪቷ ኢኮኖሚ መሰረት እንደመሆኑ ተደራሽና ጥራቱን የጠበቀ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ለማስፋት ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
የምክር ቤቱና የቋሚ ኮሚቴ አባላትና የምክር ቤቱ የሕግ ክፍል ባለሙያዎችም ረቂቅ አዋጁ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀዋል።
ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ መንግስት ቀደም ሲል በብቸኝነት በነፃ ይሰጥ የነበረውን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለምን በክፍያ መስጠት አስፈለገ የሚለው አንዱ ነው።
በሌላ በኩል የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ላይ የሚሳተፉ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የክፍያ ሥርዓትን በተመለከተ ጥያቄ ተነስቷል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) መንግስት መደበኛ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን በተደራጀና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ መስጠቱን ይቀጥላል ነው ያሉት።
ይሁንና እያደገ ያለውን የግብርና ኤክስቴንሽን ፍላጎት ለማሟላት አማራጭ አገልግሎት ሰጪዎችን ማካተት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑንም ነው ያነሱት።
የግብርና ሚኒስቴር አማካሪ ተፈራ ዘርዓይ በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ የግብርና ኤክስቴንሽን ሥራ በመንግስት ብቻ ሲከወን መቆየቱን ገልጸዋል።
የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ፣ በመንግስት ብቻ ይሰጥ የነበረውን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት በተለያዩ ወገኖች እንዲሰጥ በማድረግ ተደራሽነትን ማስፋት ያስችላል ነው ያሉት።
ይህም አሁን ላይ በግብርናው ዘርፍ እየታየ ያለውን እመርታ የበለጠ ለማሳደግና በዘርፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅና ለመጠቀም እንደሚያስችልም አብራተዋል።
ረቂቅ አዋጁ የግብርና ቢዝነስ ምንነት ላይ በቂ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠይቋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ ግብርና አንድ አዋጭ የቢዝነስ ዘርፍ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል።
ረቂቅ አዋጁ በዚህ ረገድ የግብርና ቴክኖሎጂን ማስተዋወቅና ጥቅም ላይ ማዋል እንዲሁም የግብርና ቢዝነስን ለማስፋት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ፤ ረቂቅ አዋጁ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ተደራሽነት ለማስፋት ያስችላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ለግብርና ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑንና በዚህም በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ያነሱት ሰብሳቢው፤ በተለይም በምግብ ራስን ለመቻልና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘው ግብ እውን እንዲሆን የረቂቅ አዋጁ መዘጋጀት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓም ባደረገው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል።