መንግስት ያደረጋቸው የውጪ አገር የስራ ስምሪት ስምምነቶች ውጤት እያስመዘገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ያደረጋቸው የውጪ አገር የስራ ስምሪት ስምምነቶች ውጤት እያስመዘገቡ ነው

አዲስ አበባ፤ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦መንግስት ያደረጋቸው የውጪ አገር የስራ ስምሪት ስምምነቶች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አለበል ደሴ ገለጹ።
መንግስት የውጪ አገር የስራ ስምምነቶችን በማድረግ የስራ ዕድል የሚፈልጉ ሰራተኞች ወደ መካከለኛው ምስራቅ በመጓዝ በተለያዩ የስራ ዘርፍ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት " የዓለም አቀፍ ስደት መንስኤዎች፣ ፈተናዎች እና እድሎች" በሚል ርዕስ ያካሔደውን ጥናት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ አድርጓል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አለበል ደሴ በዚሁ ወቅት፤ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ እና ከአንዱ አገር ወደ ሌላው አገር የመሰደድ የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ህገ ወጥ ስደትን ለመከላከል እያከናወናቸው ያሉ የውጭ አገር የስራ ስምሪት ስምምነት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህም ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረው፤ ነገር ግን አሁንም የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸውን አመልክተዋል።
ቀሪ ስራዎችን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪና የጥናቱ ተሳታፊ ሐና ወልደኪዳን በበኩላቸው እንደገለጹት፥ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ለህገ ወጥ ስደት የሚዳረጉት በተሳሳተ መረጃ ምክንያት ነው።
ሌላ ሀገር በመሰደድ የስራ ዕድል ብቻና ጥሩ አጋጣሚ ለሚጠብቁ መጥፎ ክስተት ሊኖር እንደሚችልም ማሳወቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።
እንዲሁም ሰዎች ከአገር ለመውጣት ህገ ወጥ መንገድ ምርጫቸው እንዳይሆን፤ለህጋዊ የውጭ አገር የስራ ስምሪት አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን በአቅራቢያቸው ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡