በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል

ደብረ ብርሃን፤ሰኔ 23/2017 (ኢዜአ)፡-በሰሜን ሸዋ ዞን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ሲል የዞኑ አስተዳደር አሰታወቀ።
"በጎነትና አንድነት ለኢትዮጵያ ከፍታ'' በሚል መሪ ሃሳብ የመጪው ክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የንቅናቄ መድረክ በደብረ ብርሃን ተካሄዷል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
በመጪው ክረምት በሚካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥና የነዋሪዎችን አብሮነት በማጠናከር ላይ ማተኮር እንዳለበት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በማህበረሰቡ ውስጥ ለዘመናት ባህል ሆኖ የቆየውን በጎ ተግባር በተደራጀ አግባብ በመምራት አረጋውያንን፣ ህጻናትንና ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምትኩ ማሙሻ በበኩላቸው በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 780 ሺህ 172 ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በመንገድ ጥገናና የአረጋዊያንን መኖሪያ ቤት በማደስና በሌሎች ልማቶች በመሳተፍ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራውም መንግስት ያወጣው የነበረውን ከ687 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ለማዳን የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ በማካሄድ ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ወጣት ፌዴሬሽን ሰብሳቢ ወጣት ዮናስ ፀጋው በበኩሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመተባበር፣ የመደጋገፍ፣ አብሮ የመስራትና በጋራ የመለወጥ ባህልን ለመማር የሚያስችል ነው ብሏል።
በመጪው ክረምት በሚካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መላ አባላትን በንቃት በማሳተፍ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድቷል።
ከሚዳ ወረሞ ወረዳ የመጣቸው የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ኤደን ተገኝ በበኩሏ አባላት የተገኘውን ሰላም ዘላቂ በማድረግ፣ በሰላምና እሴት ግንባታ ላይ በማተኮር የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን እንደሚያከናውኑ ገልጻለች።
በበጀት ዓመቱ የበጋ ወራት በተካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 405 ሺህ 429 የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ 309 ሚሊዮን 791 ሺህ ብር ግምት ያለው ተግባር መፈጸም መቻሉም ተመላክቷል።