ተማሪዎች በተዘጋጁት ልክ ፈተናውን በተረጋጋ መንፈስ መውሰድ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ተማሪዎች በተዘጋጁት ልክ ፈተናውን በተረጋጋ መንፈስ መውሰድ አለባቸው

ሆሳዕና፣ሰኔ 23/2017 (ኢዜአ)፦ ተማሪዎች በተዘጋጁት ልክ ፈተናውን በተረጋጋ መንፈስ መውሰድ እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።
እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እየወሰዱ ያሉ ተማሪዎችን አበረታተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ በሀገር አቀፍ ፈተና የተቀመጡ ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ የማጠናከሪያ ትምህርት ከመስጠት ባለፈ በሞዴል ፈተናዎች የማለማመድ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል።
ተፈታኝ ተማሪዎች በራሳቸው እንዲተማመኑም በስነልቦና የማዘጋጀት ሥራ በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።
ተማሪዎች በተዘጋጁት ልክ ፈተናውን በተረጋጋ መንፈስ መውሰድ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ግብአት ከማሟላት በተጨማሪ መምህራን ተማሪዎችን የማብቃት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም የድጋፍና ክትትል ሥራ መከናወኑንም አስታውሰዋል።
እንደ አቶ አንተነህ ገለጻ፥ በክልሉ ከ35 ሺህ በላይ ተማሪዎች ዛሬ የተጀመረውን ሀገር አቀፍ ፈተና እየወሰዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ፈተናውን በበይነ መረብ እየወሰዱ ያሉት 6 ሺህ 884 ተማሪዎች ናቸው፡፡