አዲሱ ህንጻ ዘመኑን የዋጀ፣ ጥራት ያለውና ቃል በተግባር የተገለጠበት ነው - ከንቲባ አዳነች ኤቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ ህንጻ ዘመኑን የዋጀ፣ ጥራት ያለውና ቃል በተግባር የተገለጠበት ነው - ከንቲባ አዳነች ኤቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስገንብቶ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ያስረከበው አዲሱ ህንጻ ዘመኑን የዋጀ፣ ጥራት ያለውና ቃል በተግባር የተገለጠበት መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከተማ አስተዳደሩ በመልሶ ማልማት ምክንያት በተነሳው የቤተ-ክርስቲያኗ ሕንጻ ምትክ አዲስ ያስገነባውን ሁለገብ ሕንጻ ግንባታ አጠናቆ በማስመረቅ ለቤተ-ክርስቲያኗ ዛሬ አስረክቧል።
ሕንጻው በከንቲባ አዳነች አቤቤ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በዛሬው ዕለት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የሕንጻውን ቁልፍ አስረክበዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ ሕንጻው ቃል በተግባር የተገለጸበት መሆኑን ገልጸው፤ ሕንጻው የመተማመን፣ አብሮ የመሥራትና የመተባበር ውጤት ነው ብለዋል።
በታቀደው ጊዜ ውስጥ የሕንጻው ግንባታ መጠናቀቁን ጠቁመው፤ ይህ ሕንጻ ጥራት ያለው ባለ ሰባት ወለል የተሽከርካሪ ማቆሚያም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
የሁለገብ ሕንጻው ግንባታ ሙሉ ወጪ በከተማ አስተዳደሩ የተሸፈነ መሆኑንና ግንባታው በፍጥነት፣ በጥራትና በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የኮሪደር ልማት ስራው ውጤታማ እንዲሆን ምሳሌነት ያለው ተግባር እና ውሳኔ በመወሰን የበኩሏን በማበርከት ላይ መሆኗን ገልጸው፤ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ቤተ-ክርስቲያኗ ለምታከናውናቸው ስራዎች ስኬት ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ሁልጊዜም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ የከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ ሕንጻውን በራሱ ወጪ አስገንብቶ በማስረከቡ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሕንጻው ለቤተ-ክርስቲያን አገልግሎት የሚውልና በተያዘለት ጊዜ ወቅቱን በዋጀ መልኩ መጠናቀቁንም ጠቁመዋል።
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ በበኩላቸው፤ ልማት የበጎ ሃሳብ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
ቤተ-ክርስቲያኗ የልማት ተባባሪነትና አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እውቅና እና ሽልማት አበርክታለች፡፡
የሕንጻውን ግንባታ ሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሀላፊዎች ማስጀመራቸው ይታወቃል።