በፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ ሁለት የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ ሁለት የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2017 (ኢዜአ)፦ በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ የሶስተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ምሽት 4 ሰዓት ላይ ኢንተር ሚላን ከፍሉሜኔንሴ በባንክ ኦፍ አሜሪካ ስታዲየም ይጫወታሉ።
የዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ተፈላሚ የነበረው ኢንተር ሚላን በምድብ አምስት በሰባት ነጥብ የምድቡ መሪ በመሆን ማጠናቀቀቁ የሚታወስ ነው።
ፍሉሜኔንሴ በምድብ ስድስት በአምስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብቷል።
ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም እርስ በእርስ ተገናኝተው አያውቁም።
ጨዋታው በኢንተር ሚላን የማጥቃት አቅም እና የፍሉሜኔንሴ አይበገሬ የተከላካይ ክፍል መካከል የሚደረግ ጦርነት የሚል ስያሜ አግኝቷል።
በዓለም ዋንጫው በሶስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው የ27 ዓመቱ የኢንተር ሚላን አጥቂ ላውታሮ ማርቲኔዝ እና የ40 የፍሉሜኔንሴ አንጋፋ ተከላካይ ቲያጎ ሲልቫ የሚኖራቸው ፍጥጫ ይጠበቃል።
ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ በካምፒንግ ወርልድ ስታዲየም ማንችስተር ሲቲ ከአል ሂላል ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በምድብ ሰባት የነበረው ማንችስተር ሲቲ በዘጠኝ ነጥብ ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቱ ይታወቃል። ሰማያዊዎቹ በውድድሩ የምድቡን ሁሉንም ጨዋታ ያሸነፈ ብቸኛ ክለብ ነው።
በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ ጁቬንቱስን 5 ለ 2 ሲያሸንፍ ያሳየው ድንቅ ብቃት የዋንጫ ተገማችነቱን የበለጠ አሳድጎታል።
የሳዑዲ አረቢያው አል ሂላል በምድብ ስምንት ሪያል ማድሪድን ተከትሎ በአምስት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅሏል።
ሁለቱ ክለቦች እ.አ.አ በ2012 በቅድመ ውድድር የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ተገናኝተው አል-ሂላል 1 ለ 0 አሸንፏል።
ማንችስተር ሲቲ ጨዋታውን የማሸነፍ ትልቅ ግምት ቢያገኝም ከተጋጣሚው ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል።
የጨዋታዎቹ አሸናፊዎች በሩብ ፍጻሜው የሚጫወቱ ይሆናል።
በአሜሪካ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ ዛሬ 17ኛ ቀኑን ይዟል።