አዲሱ ህንጻ የመተማመን፣ አብሮ የመሥራት እና የመተባበር ውጤት ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ ህንጻ የመተማመን፣ አብሮ የመሥራት እና የመተባበር ውጤት ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስገንብቶ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ያስረከበው ህንጻ የመተማመን፣ አብሮ የመሥራት እና የመተባበር ውጤት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመልሶ ማልማት ምክንያት በተነሳው የቤተ-ክርስቲያኗ ሕንጻ ምትክ አዲስ ያስገነባውን ሁለገብ ሕንጻ ግንባታ አጠናቆ በማስመረቅ ለቤተ-ክርስቲያኗ በዛሬው ዕለት አስረክቧል።
ሕንጻው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በዛሬው ዕለት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የሕንጻውን ቁልፍ አስረክበዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ ሕንጻው ቃል በተግባር የተገለጸበት መሆኑን ገልጸው፤ ሕንጻው የመተማመን፣ አብሮ የመሥራት እና የመተባበር ውጤት ነው ብለዋል።
በታቀደው ጊዜ ውስጥ የሕንጻው ግንባታ መጠናቀቁን ጠቁመው፤ ይህ ሕንጻ ጥራት ያለው ባለ ሰባት ወለል ሕንጻ የተሽከርካሪ ማቆሚያም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
የሁለገብ ሕንጻው ግንባታ ሙሉ ወጪ በከተማ አስተዳደሩ የተሸፈነ መሆኑን እና ግንባታው በፍጥነት፣ በጥራት እና በተያዘለት የጊዜ ገደብ የተጠናቀቀ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ የከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ ሕንጻውን በራሱ ወጪ አስገንብቶ በማስረከቡ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሕንጻው ለቤተ-ክርስቲያን አገልግሎት የሚውልና በተያዘለት ጊዜ ወቅቱን በዋጀ መልኩ መጠናቀቁንም ተናግረዋል።
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ በበኩላቸው፤ ልማት የበጎ ሃሳብ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
ቤተ-ክርስቲያኗ የልማት ተባባሪነት እና አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
የሕንጻውን ግንባታ ሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች ማስጀመራቸው ይታወቃል።