ቀጥታ፡

የካውንስሉ መመስረት ወጣቶች በእምነት እና በሀገራቸው ጉዳይ በመምከር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ያስችላቸዋል-ሸይኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ

አዳማ፤ ሰኔ 22/2017 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል መመስረት  ወጣቶች በእምነት እና  በሀገራቸው ጉዳይ በመመካከር የበኩላቸውን  አስተዋፅኦ ለማበርከት እንደሚያስችላቸው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸይኽ ሀጂ ኢብራሒም ቱፋ ገለጹ።

የኦሮሚያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ዛሬ በአዳማ ከተማ በይፋ ተመስርቷል።


 

የኦሮሚያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ዛሬ በይፋ በተሰመረተበት ወቅት ሸይኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ባስተላለፉት መልዕክት የካውንስሉ መመስረት ሙስሊም ወጣቶች ለእምነትና ለሀገራቸው በመመካከር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።


 

ወጣቶች የእምነት፤ የብሔር እና የፖለቲካ አመለካከት ሳይገድባቸው ለሀገራቸው ሰላም፣ አብሮነትና ልማት የበኩላቸውን  አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ  ምክር ቤቱ በቅርበት እንደሚደግፍም ተናግረዋል።

የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸይኽ ጋሊ ሙክታር በበኩላቸው፣ የሙስሊም ወጣቶችን መንፈሳዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ  ለማሳደግ  በክልሉ የወጣቶች ካውንስል መመስረቱን  አስታውቀዋል።


 

ካውንስሉ ለእምነቱና ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ ወጣቶችን ማፍራት እንዲቻል በቀጣይ ከዞን እስከ ቀበሌ የተሳሰረ መዋቅር ለመዘርጋት መታቀዱንም አስታውቀዋል።

በካውንስሉ ምስረታ ላይ የተገኙት የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሀይሉ ጀልዴ በበኩላቸው የካውንስሉ መመስረት ለክልሉ ሙስሊም ወጣቶች የለውጥ እና የእድገት ምዕራፍን እንደሚያበስር ገልጸዋል።


 

ካውንስሉ ወጣቱ በማህበረሰብ ውስጥ የአሰባሳቢነት፣ የመሪነትና የለውጥ ኃይል ሆኖ ሀላፊነቱን ለመወጣት እንደሚያስችለው ጠቁመዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከካውንስሉ ጋር በቅርበት  በመስራት የወጣቶች  እንቅስቃሴን  ለማጎልበት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

ዛሬ የተመሰረተው የኦሮሚያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል 11 የሥራ አስፈጻሚ አባላት ያሉት ሲሆን ወጣት ሹሀብ ሸምሱ የካውንስሉ ሰብሳቢ ሆኖ ተመርጧል።

በካውንስሉ ምስረታ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ወጣቶች፣ ዑለማዎች፣ የማህበረሰብ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም