ኢንተር ሚያሚ ፒኤስጂን በማሸነፍ ዓለምን ያስደምም ይሆን?

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2017 (ኢዜአ)፦  በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ፒኤስጂ እና ኢንተር ሚያሚ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ጨዋታው ምሽት 1 ሰዓት ላይ በሜርሴዲስ ቤንዝ ስታዲየም ይደረጋል።

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ፒኤስጂ በነበረበት ምድብ ሁለት በስድስት ነጥብ የምድቡ መሪ በመሆን አጠናቋል።

ኢንተር ሚያሚ በምድብ ሁለት በአምስት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ወደ 16 ውስጥ ገብቷል። 

ሁለቱ ክለቦች እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው።

የኢንተር ሚያሚው አምበል እና አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ከቀድሞ ክለቡ ፒኤስጂ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ የዓለምን ትኩረት ስቧል። 

ሜሲ ከእ.አ.አ 2021 እስከ 2023 በፓሪሱ ክለብ የቆየ ሲሆን በቡድኑ በነበረው ቆይታ ደስተኛ እንዳልሆነ ገልጾ ነበር። 

ጨዋታው አርጀንቲናዊው ምትሃተኛ ፒኤስጂ ለሱ የሰጠው ግምት ትክክል አለመሆኑን  የሚያሳይበት መልካም አጋጣሚ ፈጥሮለታል።

የኢንተር ሚያሚው አሰልጣኝ ሃቪየር ማሻራኖ ሜሲ ከቀድሞ ክለቡ ጋር በንዴት መጫወቱ እኛን ይጠቅመናል፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ምርጥ ብቃቱን የበለጠ አውጥቶ ያሳያል ሲል ገልጿል። 

ሜሲ፣ ማሻራኖ፣ ራሞን ጆርዲ አልባ እና ሉዊስ ሱዋሬዝ በባርሴሎና አሰልጣኛቸው ከነበሩት የአሁኑ የፒኤስጂ አለቃ ሉዊስ ኤነሪኬ ጋር ይገኛሉ።

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ፒኤስጂ ጨዋታውን የማሸነፍ ሰፊ ግምት አግኝቷል። 

ቡድኑ ባለው በጠንካራ ተከላካይ ክፍሉ እና በአስፈሪው የፊት መስመር ታግዞ ጨዋታውን እንደሚያሸንፍ የኳስ ልሂቃኑ በመናገር ላይ ይገኛሉ።

ለጥቃት ተጋላጭ የተከላካይ ክፍል መስመር ያለው እና በውስን ተጫዋቾች ብቃት ላይ የተንጠለጠለው ኢንተር ሚያሚ ማንም ያልጠበቀውን ድል ሊያስመዘግብ ይችላል የሚሉ ተንታኞችም አልጠፉም።

ሌላኛው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ፍላሚንጎ እና ባየር ሙኒክን ምሽት 5 ሰዓት ላይ በሃርድ ሮክ ስታዲየም ያገናኛል። 


 


 

ፍላሚንጎ በምድብ አራት በሰባት ነጥብ አንደኛ፣ ባየር ሙኒክ በምድብ ሶስት በስስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወቃል።

የታክቲክ ጦርነት ይደረግበታል በተባለበት በዚህ ጨዋታ ፍላሚንጎ ፈጣን የማጥቃት ሽግግሩ እና ኳስ ይዘው የሚጫወቱት አማካዮቹ በጨዋታው ላይ ልዩነት እንደሚፈጥሩ እየተነገረ ይገኛል።

ባየር ሙኒክ ጥራት ያላቸውን ተጫዋቾች ሰብስቦ መያዙ እና የቡድን ጥልቀቱ በአንጻራዊነት የማሸነፍ እድል እንዲሰጠው አድርጎታል። 

የዛሬ ጨዋታ አሸናፊዎች በሩብ ፍጻሜው ይገናኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም