ቼልሲ ሩብ ፍጻሜ ገብቷል

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 22/2017(ኢዜአ)፦ በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ ሁለተኛ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ ቼልሲ ቤኔፊካን 4 ለ 1 አሸንፏል።

ትናንት ማምሻውን በባንክ ኦፍ አሜሪካ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሪስ ጀምስ በ64ኛው ደቂቃ በግሩም ሁኔታ በቅጣት ምት ያስቆጠራት ግብ ቼልሲን መሪ አድርጓል።

ጨዋታው በ86ኛው ደቂቃ ላይ በመጥፎ የአየር ንብረት ምክንያት ለሁለት ሰዓታት ተቀርጦ ነበር።

ጨዋታው በድጋሚ ከተጀመረ በኋላ በ95ኛው ደቂቃ አንጌል ዲማሪያ በፍጹም ቅጣት ያስቆጠራት ጎል ቤኔፊካን አቻ አድርጓል።

ቡድኖቹ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ አቻ በመለያየታቸው ወደ ጭማሪ 30 ደቂቃ አምርተዋል።

በተጨማሪ ሰዓት ክርስቶፈር ንኩኩ በ108ኛው፣ ፔድሮ ኔቶ በ115ኛው እና ኬይርናን ዴውስበሪ-ሆል በ117ኛው ደቂቃ ያስቆጠሯቸው ግቦች ቼልሲ ተጋጣሚው አሸንፏል።

ውጤቱን ተከትሎ ቼልሲ ሩብ ፍጻሜው የተቀላቀለ ሁለተኛ ቡድን ሆኗል።

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ በሩብ ፍጻሜው ከፓልሜራስ ጋር ይጫወታል።

ፓልሜራስ ትናንት በጥሎ ማለፉ የመጀመሪያ ጨዋታ ቦታፎጎን 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወቃል።

የቼልሲ እና ቤኔፊካ ጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር በዓለም ዋንጫው በመጥፎ የአየር ንብረት ምክንያት የተቋረጠ ሰባተኛ ጨዋታ ነው።

ከፍተኛ ሙቀት እና መብረቅ ለጨዋታዎች መቋረጥ ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው።

ጨዋታዎች መቋረጣቸው የተጫዋቾችን ደህንነት ለመጠበቅ ያስችላል የሚል ሙገሳ ቢያገኝም ለረጅም ሰዓታት መቆሙ የጨዋታዎች ድባብ እና ፉክክር ላይ ጥላ አጥልቷል የሚል ትችትም እንዲያስተናግድ አድርጓታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም