ፓልሜራስ በፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለ የመጀመሪያ ቡድን ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
ፓልሜራስ በፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለ የመጀመሪያ ቡድን ሆኗል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2017(ኢዜአ)፦ በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ ፓልሜራስ ቦታፎጎን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በሊንከን ፋይናንሻል ፊልድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሁሉቱ የብራዚል ቡድኖች በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተው ወደ ተጨማሪ 30 ደቂቃ አምርተዋል።
ተቀይሮ የገባው የ24 ዓመቱ ብራዚላዊ አጥቂ ፓውሊኒዮ በ100ኛው ደቂቃ ላይ በድንቅ አጨራረስ ያስቆጠራት ግብ ፓልሜራስን ባለድል አድርጋለች።
የፓልሜራስ አምበል ጉስታቮ ጎሜዝ በ116ኛው ደቂቃ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
በጨዋታው በኳስ ቁጥጥር እና የግብ እድል በመፍጠር ፓልሜራስ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል። ቦታፎጎ በአመዛኙ መከላከል ያመዘነ የጨዋታ እንቅስቃሴ አድርጓል።
ውጤቱን ተከትሎ ፓልሜራስ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለ የመጀመሪያው ቡድን ሆኗል። በሩብ ፍጻሜው ከቤኔፊካ እና ቼልሲ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
ቤኔፊካ ከቼልሲ ምሽት 5 ሰዓት ላይ በባንክ ኦፍ አሜሪካ ስታዲየም ይጫወታሉ።