የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ለማሳካት ችግር ፈቺ ምርምሮችን ወደ ተግባር የመለወጥ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ለማሳካት ችግር ፈቺ ምርምሮችን ወደ ተግባር የመለወጥ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት፣ ስራ ስምሪትና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አመራሮች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ተመራማሪዎች፣ የፈጠራ ባለሙያዎችና የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች የተሳተፉበት የምርምርና ኢኖቬሽን አውደ ጥናት መካሄድ ጀምሯል።


 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ትልቅ ህልም ሰንቃ የዜጎችን ህይወት ሊቀይሩ የሚችሉ የልማት ስራዎች ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች።

ሁለንተናዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጡ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች እንዲበራከቱ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን የማሻሻል ስራ መሰራቱንም አስታውቀዋል።

በተከናወኑ ተግባራት ሁለንተናዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጡ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለያዘችው የልማት ጉዞ የምሁራን የጥናትና ምርምር ስራዎች መሬት ላይ ወርደው የዜጎችን ህይወት መቀየር እንዲችሉ የሚሰራው ስራ መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ መንግስት ባለፉት ዓመታት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉን በማጎልበት ወጣቶችን በፈጠራ ስራዎች በሰፊው ለማሳተፍ መስራቱን ገልጸዋል፡፡

በሳይንስና ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ሊበራከቱ እንደሚገባም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም