የእንጦጦ ማርያም፣ ስፔስ ኦብዘርቫቶሪ-ኮተቤ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ አፈጻጸም ከ67 በመቶ በላይ ደርሷል - አስተዳደሩ - ኢዜአ አማርኛ
የእንጦጦ ማርያም፣ ስፔስ ኦብዘርቫቶሪ-ኮተቤ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ አፈጻጸም ከ67 በመቶ በላይ ደርሷል - አስተዳደሩ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2017(ኢዜአ)፦ የእንጦጦ ማርያም፣ ስፔስ ኦብዘርቫቶሪ-ኮተቤ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ አፈጻጸም ከ67 በመቶ በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ከእንጦጦ ማርያም-ጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታም እየተፋጠነ ይገኛል።
ኢዜአ የመንገድ ፕሮጀክቶችን የግንባታ ሥራ ቅኝት በማድረግ የፕሮጀክቶቹ ኃላፊዎችንና የአካባቢውን ነዋሪዎች አነጋግሯል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የማዕከላዊ ሪጅን ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ፕሮግራም ቡድን መሪ ኢንጂነር ዳዊት በላይ፤ ከእንጦጦ ማርያም በስፔስ ኦበዘርቫቶሪ እስከ ኮተቤ እየተገነባ ያለው የመንገድ ፕሮጀክት እየተፋጠነ ነው ብለዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ 18 ነጥብ 58 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 31 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን የግንባታ አፈጻጸሙም 67 ነጥብ 55 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት፡፡
በቀጣይ ዓመት ህዳር ወር ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው ጨምረው የተናገሩት፡፡
የመንገዱ መጠናቀቅ የሸገር ከተማን ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በማስተሳሰር የተቀናጀ የኢኮኖሚና የልማት እንቅስቃሴ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ከለገጣፎ በኩል አዲስ አበባን አቋርጠው የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ወደ መሃል ከተማ ሳይገቡ ወደ ሱሉልታ መውጫ የሚጓዙበትን ዕድል እንደሚፈጥርም አንስተዋል።
ይህም በአዲስ አበባ የሚኖረውን የትራፊክ መጨናነቅ በመቀነስ በኩል ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አዲሱ ፈንታው በበኩላቸው የመንገዱ የመጀመሪያ የአስፋልት ንጣፍ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የአስፋልት ድረባ ስራ እንዲሁም የእግረኛ መንገድ እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፥ በተያዘለት ቀነ ገደብ ይጠናቀቃል ነው ያሉት።
በተመሳሳይ ከእንጦጦ ማርያም ጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል የ4 ነጥብ 37 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክት በፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ቢኒያም ኃ/ገብርኤል ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት ግንባታው 57 በመቶ መድረሱንና ከተያዘለት ጊዜ ቀደም ብሎ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የእንጦጦ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ዝናሽ ወኒንጁ ከእንጦጦ ማርያም እስከ ኮተቤ እየተገነባ ያለው መንገድ ለማህበረሰቡ ትልቅ እፎይታን የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
የከባድ ጭነት መኪና አሽከርካሪ የሆኑት ከተማው ደመቀ በበኩላቸው፥ ሁለቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች የትራንስፖርት ፍሰቱን ለማሳለጥ እንዲሁም ሀገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች ወደ መሃል ከተማ ሳይገቡ በቀጥታ ወደ መዳረሻቸው የሚጓዙበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።