'ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ' የተባለውን መጤ አረም ለሲሚንቶ ማምረቻነት በኃይል አማራጭነት ለመጠቀም የሚያስችል ጥናትና ምርምር ተጠናቆ ወደ ስራ ተገባ - ኢዜአ አማርኛ
'ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ' የተባለውን መጤ አረም ለሲሚንቶ ማምረቻነት በኃይል አማራጭነት ለመጠቀም የሚያስችል ጥናትና ምርምር ተጠናቆ ወደ ስራ ተገባ
ድሬደዋ ፣ ሰኔ 21/2017 (ኢዜአ):-በሳይንሳዊ ስሙ 'ፕሮሶፒስ ጁሊ ፍሎራ' የተባለውን መጤ አረም ለሲሚንቶ ማምረቻነት በኃይል አማራጭነት ለመጠቀም ሲደረግ የነበረው ጥናት ተጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሳይንሳዊ ስሙ ፕሮሶፒስጁሊ ፍሎራ የተባለውን መጤ አረም ወደ ኃይል በመለወጥ ለሲሚንቶ ማምረቻነት ለማዋል እንዲቻል በተደረገ ጥናት ላይ ውይይትና የልምድ ልውውጥ ዛሬ በድሬዳዋ ተካሄዷል።
'ፕሮሶፒስ' በመባል በአጭሩ የሚጠቀሰው መጤ አረሙ በኢትዮጵያ በአብዛኛው ተደጋጋሚ ድርቅ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች በስፋት ተንሰራፍቶ ይገኛል።
አረሙ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች በብዛት ተንሰራፍቶ ሲገኝ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎችም በተወሰኑ አካባቢዎች ይገኛል
በኢትዮጵያ በጠቅላላው በ2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘው አረሙ በተለይ በሶማሌና በአፋር ክልሎች የግጦሽና የእርሻ መሬትን በመውረር ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።
በመሆኑም አረሙን በማጨድና በመፍጨት ለኃይል አማራጭነት በማዋል ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንደ ድንጋይ ከሰል በመሆን አገልግሎት እንዲሰጥ ጥናት ሲደረግ ቆይቷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሐሰን መሐመድ እንዳሉት፤ መጤ አረሙ ለሲሚንቶ ማምረቻነት በኃይል አማራጭነት ለመጠቀም የሚያስችል ጥናትና ምርምር ተጠናቆ ወደ ስራ ተገብቷል።
በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ተንሰራፍቶ የሚገኘውን መጤ አረም ጥቅም ላይ ለማዋል በሙከራ ደረጃ በተጀመረው ስራ 2 ሺህ 200 ሄክታር መሬትን ከአረሙ ነፃ በማድረግ ለመስኖ እንዲውል ተደርጓል ብለዋል።
ይህም የአርብቶና አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግና የስራ ዕድል ተጠቃሚነት እንዲጨምር ማስቻሉን አመልክተዋል።
በተጨማሪም 29 ሺህ ቶን ባዮማስ በማምረት በውጭ ምንዛሬ ይገባ የነበረውን 14 ሺህ 500 ቶን የድንጋይ ከሰል ማስቀረት መቻሉን አስታውቀዋል ።
በዚህም ለድንጋይ ከሰል ይወጣ የነበረን ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማስቀረት መቻሉን ገልፀዋል።
በሙከራ ደረጃ በናሺናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የተጀመረውን ለአገር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርገውን ይህንኑ አዋጭ ፕሮጀክት ወደ ሌሎች የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማስፋት ስራ መጀመሩንም አስረድተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው መጤ አረምን ወደ ጥቅም የመለወጥ ፕሮጀክት የተጀመረውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያስችላል ብለዋል።
በተለይ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለድንጋይ ከሰል ያወጡት የነበረውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት መፍትሄ ከመስጠት ባሻገር ምርትና ምርታማነትን እንደሚጨምርም ጠቁመዋል።
በውይይቱና በልምድ ልውውጡ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራር አባላት፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ስራ አስኪያጆችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ከውይይቱ በኋላም በናሺናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ምልከታ እንደሚከናወንም ተገልጿል።