የጉራጌን የባህል እሴቶች ጠብቆ በማቆየትና የሀገር ሃብት አድርጎ ለመጠቀም የተቀናጀ ጥረት ሊደረግ ይገባል-- ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የጉራጌን የባህል እሴቶች ጠብቆ በማቆየትና የሀገር ሃብት አድርጎ ለመጠቀም የተቀናጀ ጥረት ሊደረግ ይገባል-- ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ወልቂጤ ፤ሰኔ 21 /2017 (ኢዜአ)፡- የጉራጌን የባህል እሴቶች ጠብቆ በማቆየትና የሀገር ሃብት አድርጎ ለመጠቀም የተቀናጀ ጥረት ሊደረግ ይገባል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ተናገሩ ።
የጉራጌ የባህል እና ቋንቋ ሲምፖዚየም ርእሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ የጉራጌ ባህላዊ እሴቶችን የሚያሳይ ኢግዚቢሽን ለእይታ የቀረበ ሲሆን በጀፎረ ዙርያ የተዘጋጀ ጥናታዊ ፅሁፍ እና የአካባቢውን ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት የሚያሳይ ቴአትር እንደሚቀርብ ይጠበቃል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፤ የጉራጌ የአብሮነትና እምቅ ባህላዊና የተፈጥሮ እሴቶች ተጠብቀው መዝለቃቸውን አንስተው በቀጣይም የሀገር ሃብትና የትውልድ ውርስ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ አሁን ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ባህላዊ እሴቶችን የመጠበቅ፣ የመንከባከብና በጥናትና ምርምር የታገዘ ቀጣይነት ያለው ስራ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የጉራጌን እምቅ ባህላዊና የተፈጥሮ እሴቶች ጠብቆ በማቆየትና የሀገር ሃብት አድርጎ ለመጠቀም የሁሉንም ጥረትና እገዛ ይጠይቃል ብለዋል።
ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማስጠበቅ የጋራ ሀገራዊ ብልጽግና እውን እንዲሆን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የራሱን አሻራ እያኖረ መሆኑን አንስተው ሁለንተናዊ ስራው ቀጣይነት እንደሚኖረውም አረጋግጠዋል።
የጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ፤ የጉራጌን ባህልና ቋንቋ በጥናትና ምርምር የማሳደግ እና ጠብቆ የማቆየት ስራ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።
የጉራጌ የባህል እና የቋንቋ ሲምፖዚየም ዋነኛ አላማም የጉራጌ ህዝብ የባህል እሴት እና ትውፊቱ ተጠብቆ እንዲቆይና ለትውልዱ እንዲተላለፍ የማድረግ ጥረት አካል መሆኑን አንስተዋል።
የጉራጌን ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ በተመለከተ ጥልቅ ግንዛቤ መፍጠር ምሁራንና ተመራማሪዎች ተጨማሪ ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ የማበረታታት አላማ የሰነቀ መሆኑንም አስረድተዋል።