ቀጥታ፡

የህብረት ስራ ማህበራት ለስራ ዕድል ፈጠራና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2017(ኢዜአ)፦ የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ለስራ ዕድል ፈጠራና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስተባባሪነት በአዲስ አበባ ሲያካሄድ የቆየው የ2025 የአፍሪካ የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት አመታዊ ጉባዔ ተጠናቋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፣ የአፍሪካ የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን በአፍሪካ ውስጥ ያሉ የቁጠባና ብድር ማህበራትን የሚያስተባብር ተቋም ነው ብለዋል፡፡

በጉባዔው በፋይናንስ አሰራር ማዕቀፍና በፋይናንስ ደህንነት እንዲሁም ቁጥጥር ስርዓት ዙሪያ በመወያየት አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡

ወደ ፊት የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት አሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን በትብብር ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ 110ሺህ የህብረት ስራ ማህበራት እንደሚገኙ ገልጸው፤ ከእነዚህ ውስጥ 23ሺህ የሚሆኑት የቁጠባና ብድር ማህበራት ናቸው ብለዋል፡፡

እነዚህ የቁጠባና ብድር ማህበራት በአጠቃላይ 8ነጥብ 5 ሚሊዮን አባላትና 50 ቢሊዮን ብር ቁጠባና ካፒታል እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ማህበራቱ ለስራ ዕድል ፈጠራና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አንስተዋል፡፡

በዚህም መንግስት እነዚህን ማህበራት የበለጠ ለማስፋትና አሰራራቸውን ለማዘመን በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡


 

የአፍሪካ የትብብር፣ ቁጠባና ብድር ማህበራት ኮንፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር ጆርጅ ኦምባዶ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ እስካሁን ያልተነኩ ብዙ የዕድገት አመራጮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ይገኙበታል ነው ያሉት፡፡

የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ከዘንድሮው የአፍሪካ የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ጉባዔ ከቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት በሚፈለገው ልክ መጠቀም የሚያስችል ግብዓት መገኘቱንም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዘርፉ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ለቀሪ የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ተሞክሮ የሚወሰድባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

በጉባዔው ከ24 ሀገራት የተውጣጡ ከ150 በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም