ቀጥታ፡

በርካታ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ለመሳተፍ ጥያቄ እያቀረቡ ነው - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት የባንክ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረጉን ተከትሎ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ለመሳተፍ ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ፡፡

አቶ ማሞ ምህረቱ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት የማድረግ ሂደትን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ለማድረግ መንግሥት የፖሊሲ እርምጃ መውሰዱን አንስተዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ አቅጣጫውን ወደ ተግባር የሚለውጥ አዋጅ በማውጣት ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የውጭ የፋይናንስ ኢንቨስትሮችና በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የራሳቸውን ተቀጥላ ወይም ሰብሲደሪ ባንክ በማቋቋም፣ ከሀገር ውስጥ ባንኮች ድርሻ፣ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በመክፈት እንዲሁም የውክልና ቢሮዎችን በማቋቋም መግባት እንደሚችሉ በአዋጁ ተመላክቷል ብለዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚፈቅድ ዝርዝር መመሪያ ማውጣቱንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ለማድረግ የፈቃድ አሰጣጥና የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን አንስተዋል።

የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ተቋማት ክፍት መደረጉ ለሀገር ትልቅ ፋይዳ ይዞ እንደሚመጣም ነው ገዥው የጠቆሙት።

ለአብነትም በፋይናንስ ዘርፉ ያለውን ካፒታል ለማሳደግ፣ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ፣ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ ዲጂታል የባንክ ስርዓትን ለማስፋፋትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ያስችላል ነው ያሉት።

በርካታ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ለመሳተፍ ጥያቄ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፥ ብሔራዊ ባንክም ፈቃድ ለመስጠት ጥያቄያቸውን እየተቀበለ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የጎረቤት ሀገራትና የመካከለኛው ምስራቅ ባንኮች ፍላጎታቸውን እያሳዩ መሆኑን ገልጸው፥ ባንኮቹ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እሴት የሚጨምሩና የፋይናንስ ዘርፉን ይበልጥ ጠንካራ የሚያደርጉ ከሆኑ እንዲሰማሩ ይደረጋል ብለዋል።

ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት የማድረግ ዋና ዓለማው ብድርን ወደ ኢንቨስትመንት ለማሸጋገር፣ አካታችነትን ለማጠናከርና ኢኮኖሚው ይበልጥ ምርታማ እንዲሆን ለማስቻል መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም