ቀጥታ፡

ተመራቂ ተማሪዎች የኢትዮጵያን ፍላጎትና ብሔራዊ ጥቅም መሠረት በማድረግ በታማኝነት ማገልገል ይጠበቅባችኋል - ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2017(ኢዜአ)፦ ተመራቂ ተማሪዎች የኢትዮጵያን ፍላጎትና ብሔራዊ ጥቅም መሠረት በማድረግ ሀገራችሁን በታማኝነት ማገልገል ይጠበቅባችኋል ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 6ሺህ 849 ተማሪዎች አስመርቋል።


 

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የበርካታ ምሁራን መፍለቂያ ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ልህቀት ብቻ ሳይሆን የጥበብ፣ የታሪክና ቅርስ ማህደር ጭምር ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ለሀገር ውስጥ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን አለም አቀፍ ዜጎችን በመሳብ የእውቀት ማዕከል ሆኖ እያገለገለ መሆኑንም አብራርተዋል።


 

በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ስራውን ይበልጥ በማጠናከር ተወዳዳሪና ተመራጭ ለማድረግ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በጠንካራ የትምህርት ሃብት በጥበብ የተሰራችሁ ተመራቂዎች የዓመታት ድካማችሁንና ልፋታችሁን በተግባር ለማዋል ዝግጁ መሆን አለባችሁ ብለዋል።

በስራ አለም የሚኖር ቆይታ የአለምን ተለዋዋጭ ሁኔታ በመረዳት የኢትዮጵያን ፍላጎትና ብሔራዊ ጥቅም መሠረት በማድረግ ሀገራችሁን በታማኝነት ማገልገል ይጠበቅባችኋል ነው ያሉት፡፡


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዘንድሮ የተማሪዎች ምረቃ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ከሆነ በኋላ የመጀመሪያ የምረቃ በዓል መሆኑ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።

በዚህ ሒደት ዩኒቨርሲቲው አሰራሩን በማሻሻል፣ የመማር ማስተማር ስራውን ለማጠናከር ባካሔደው የሪፎርም ስራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

በተለይም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ የትምህርት ስርዓት ተግባራዊ መደረጉ ዩኒቨርሲቲው ያለውን ላቅ ያለ አፈፃፀም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ጉልህ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።

በመሆኑም በ2017 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመረቃችሁ ተማሪዎች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ስጦታዎች ናችሁ ብለዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች ለዚህ ስኬት እንድትበቁ ኢትዮጵያ ጥሪቷንና ተስፋዋን በእናንተ ላይ አውላለች ሲሉም ገልጸዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጉዞ ከዳር ለማድረስ ሀላፊነት ተጥሎባችኋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም