በፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
በፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2017 (ኢዜአ)፦በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ ወደ ሩብ ፍጻሜ የሚገቡ ቡድኖች የሚለዩባቸው የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ።
ምሽት 1 ሰዓት ላይ ፓልሜራስ ከቦታፎጎ በሊንከን ፋይናንሻል ፊልድ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ፓልሜራስ በምድብ አንድ በአምስት ነጥብ አንደኛ፣ ቦታፎጎ በምድብ ሁለት በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
ሁለቱ የብራዚል ክለቦች በዘንድሮው ውድድር ጠንካራ ብቃታቸውን እያሳዩ ይገኛል። ቦታፎጎ በምድቡ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊውን ፒኤስጂን 1 ለ 0 ያሸነፈበት ውጤት ያልተጠበቀ ነበር።
ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 106 ጊዜ ተገናኝተው ፓልሜራስ 40 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ቦታፎጎ በ32ቱ ድል ቀንቶታል። 34 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።
በመጋቢት ወር በብራዚል ሴሪአ ባደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱ የብራዚል ጠንካራ ቡድኖች ተመጣጣኝ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሁለተኛው የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ ቤኔፊካ ከቼልሲ በባንክ ኦፍ አሜሪካ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ቤኔፊካ በምድብ ሶስት በሰባት ነጥብ የምድቡ መሪ በመሆን አጠናቋል። ቼልሲ በምድብ አራት በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል።
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች ቼልሲ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።
እ.አ.አ በ2013 በዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ ተገናኝተው ቼልሲ 2 ለ 1 በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳቱ የሚታወስ ነው።
በሩብ ፍጻሜው የፓልሜራስ እና ቦታፎጎ አሸናፊ ከቤኔፊካ እና ቼልሲ አሸናፊ ጋር ይጫወታሉ።
የፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር እስከ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) አስታውቋል።