በጤና ተቋማት ጥራት ያለውን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው -የክልሉ ጤና ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በጤና ተቋማት ጥራት ያለውን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው -የክልሉ ጤና ቢሮ
አዳማ ፤ሰኔ 21/2017(ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል በመሰረታዊ የጤና ተቋማት ጥራት ያለውን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ የመሰረታዊ ጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የሚያስችል የምክክር መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ፕሮፌሰር ነፃነት ወርቅነህ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት በክልሉ በመሰረታዊ የጤና ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲረጋገጥ እየተሰራ ነው።
በተለይ ከጤና ኬላ ጀምሮ በጤና ጣቢያዎችና በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የጤና አገልግሎት አሰጣጥን የተሳለጠ ለማድረግ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።
የህክምና መሳሪያዎችና መድ`ኃኒቶች አቅርቦት፣ ብቁ የሰው ኃይል የማሟላት እንዲሁም የሪፌራል አሰራሩን ማጠናከር በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በስነ-ምግባር የታነፁና የአገልጋይነት መንፈስ የተላበሱ ሙያተኞችን ለማፍራት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸው በዚህ ረገድ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የዛሬው መድረክም ከጤና ኬላ ጀምሮ ጤና ጣቢያና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን በማስተሳሰር የተሻለ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር የልምድ ልውውጥ ጭምር ለማድረግ የታለመ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው በዞኑ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን የተሻለ ለማድረግ አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
የጤና ተቋማት የፋይናንስ አቅማቸውን ለማጠናከር እንዲችሉ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን አመልክተው ሌሎች የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያሻሽሉ ስራዎች ጎን ለጎን እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ 217 ሺህ የጤና መድህን ተጠቃሚ ማፍራት መቻሉን የገለፁት አቶ አባቡ እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት በርካታ ጤና ኬላዎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አውስተዋል።
በተጨማሪም በዞኑ ለሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ከ60 በላይ የአልትራሳውንድና የላቦራቶሪ ማሽኖች ተገዝተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ ከተለያዩ የክልሉ ዞኖች የተወጣጡ በየደረጃው የሚገኙ የጤና ዘርፍ አመራሮችና ሙያተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።