ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሁሉም ሀገራት አርአያ የሚሆን ነው -የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 20/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  ለአየር ንብረት ለውጥ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት ለሁሉም ሀገራት አርአያ የሚሆን ነው ሲሉ  የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ውጥን እንዲሳካ በማድረግ ረገድ የዘመናዊ አመራር ተምሳሌት መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

የናይጄሪያው ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሼቲማ፤ “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር  ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያ የአየር ንብረትን ለውጥ ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ በሚያበረክተው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እያስመዘገበች ያለውን ለውጥ አድንቀዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ አደጋን የደቀነ እና ተግባራዊ እርምጃ የሚያስፈልገው የጋራ ጉዳያችን ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ለችግሩ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት አብነት የሚሆን ስራ ማከናወኗን ገልጸዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ራዕይና ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ በአፍሪካ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የያዙ ሀገራት መሆናቸውን የተናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ይህም  ሁለቱ ሀገራት የጋራ ህልም ይዘው ለአፍሪካ የተሻለ እጣ ፋንታ መስራት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ከሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች መሆኑ ደግሞ ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ውጥን እንዲሳካ በማድረግ ረገድ የዘመናዊ አመራር ተምሳሌት መሆናቸውንም አንስተዋል።
#ጽዱኢትዮጵያ 
#አካባቢጥበቃ 
#አረንጓዴአሻራ 
#Ethiopian_News_Agency 
#ኢዜአ 
#Ethiopia 
#ኢትዮጵያ 
#አረንጓዴ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም