ቀጥታ፡

በጌዴኦ ዞን ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ ለህዝብ የልማት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ይሰራል--አስተዳደሩ

ዲላ፤ ሰኔ 20/2017 (ኢዜአ)--በጌዴኦ ዞን ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ ለህዝብ የልማት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

በዞኑ የ2017 የግብር ዘመን ግብር ክፍያ እና የ2018 የንግድ ሥራዎች ፈቃድ ዕድሳት ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።


 

የዞኑ አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት የዞኑ ገቢ የመሰብሰብ አቅም በየጊዜው እያደገ በመምጣቱ  ለህዝብ የልማት ፍላጎት ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።

ለዚህም በሁሉም የገቢ አማራጮች ገቢን አሟጦ መሰብሰብና ግብይትን በደረሰኝ ብቻ እንዲፈጸም  ተገቢ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሐምሌ 1 የሚጀመረው የደረጃ "ሐ" ግብር ክፍያ ለዓመቱ የገቢ ዕቅድ መሳካት መሰረት ነው ያሉት አስተዳዳሪው፣ ክፍያውን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በዘመቻ ለማጠናቀቅ በቅንጅት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ለዚህም የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማጠናከርና ዘመናዊ አሰራሮችን በመዘርጋት ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ግብሩን በወቅቱ እንዲከፍል ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።


 

ከጌዴኦ ዞን ባለፉት 11 ወራት ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ያነሱት ደግሞ የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ሃላፊ አቶ ጌቱ ታምሩ ናቸው።

ይህም ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

በተለይ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች በአንድ ማዕከል ግብራቸውን በተቀላጠፈ መንገድ እንዲከፍሉ መደረጉ ለገቢው  እድገት መንስኤ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ ወደ ማዕከላት በመምጣት ግብራቸውን በወቅቱ እንዲከፍሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የጌዴኦ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት ያሬድ በበኩላቸው፣ ከደረጃ "ሐ" የግብር ከፍያ በተጓዳኝ ከሐምሌ 1 ጀምሮ የንግድ ፍቃድ እድሳት በቅንጅት እንደሚሰጥ ጠቅስዋል።

ለዚህም በዞኑ ሁሉም መዋቅሮች የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጡ 31 ማዕከላት ዝግጁ መደረጋቸውን ነው ያነሱት።

በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥም ከ15 ሺህ ለሚልቁ የንግዱ ማህበረሰብ የንግድ ፍቃዳቸውን ለማደስ መታቀዱንም ተናግረዋል።

በመድረኩ የዞኑና የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም