የጸዳችና ለኑሮ ምቹ የሆነች ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል - ባለስልጣኑ

ሀዋሳ፤ ሰኔ 20/2017(ኢዜአ)፦ የጸዳችና ለኑሮ ምቹ የሆነች ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የኢፌዴሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስገነዘበ።

በሲዳማ ክልል "ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ" በሚል መሪ ሃሳብ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚካሄድ 2ኛው የንቅናቄ መርሃ ግብር በይፋ ተጀምሯል።


 

የህዝብ ንቅናቄ መርሃ ግብር መጀመሩን አስመልክቶ በሀዋሳ ከተማ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የኢፌዴሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ፤ የጸዳችና ለኑሮ ምቹ የሆነች ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ባህል አድርጎ መውሰድ እንዳለበት አንስተዋል።

ከብክለት ጋር ተያይዞ የሚመጡ የጤና እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ለሰዎች ፈተና በመሆናቸው በተቀናጀ መንገድ ጽዱ ኢትዮጵያን መፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ተጨባጭ ውጤት እየመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በዛሬው እለት በይፋ ለተጀመረው ንቅናቄ መሳካት የክልሉ ህዝብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደረግ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው የአካባቢ ብክለት የመከላከል አጀንዳ የሁሉንም ሰው ተሳትፎ የሚጠይቅ የጋራ አጀንዳችን ሆኖ ይከናወናል ብለዋል።

በክልሉ ቆሻሻን በማጽዳት ንፁህ አካባቢን ከመፍጠር ባለፈ በማሰባሰብና በመለየት መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ጥረትም በልዩ ትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

በመሆኑም በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው ሁለተኛው ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ መርሃ ግብር እንዲሳካ በየደረጃው ያለ አመራርና አጠቃላይ ህብረሰተቡ የድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም