ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እየተገበረ ያለውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ማጠናከር አለበት - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እየተገበረ ያለውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ማጠናከር አለበት - ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እየተገበረ ያለውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አጠናክሮ እንዲያስቀጥል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ።
ቋሚ ኮሚቴው የባንኩን የ2017 በጀት ዓመት የ11 ወራት የሥራ አፈፃፀም ገምግሟል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የተቋሙን የገንዘብ ፖሊሲ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ስለ ተወሰዱ እርምጃዎች፣ የውጭ ምንዛሬ ሪፎርሙ ያስገኘውን ውጤት ጨምሮ የባንኩን የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል።
በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችሉ የሪፎርም ተግባራትን ማከናወኗን ነው ያብራሩት።
በተያዘው በጀት ዓመት የኢኮኖሚ ጫናን በመቋቋም በፊሲካልና በገንዘብ ፖሊሲ እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ ግኝት ውጤታማ ስራ አከናውናለች ብለዋል።
የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት በኩል ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተው፣ ባንኩ በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ምንም አይነት ብድር ለመንግስት አለመስጠቱን አመልክተዋል።
የዋጋ ንረቱ በዘላቂነት መፍትሔ እስኪያገኝም ባንኩ የሚከተለውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከ50 ዓመታት በላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሲደረግበት የነበረው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርዓት በገበያ እንዲወሰን በመደረጉ ትልቅ ስኬት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
በዚህም በህጋዊ እና በትይዩ ገበያው መካከል የነበረውን ከፍተኛ ልዩነት በማጥበብ ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው የውጭ ምንዛሬ እንዲጨምር ማድረጉን ነው ያብራሩት።
በአሁኑ ጊዜ የባንክ ዘርፉ በሁሉም መመዘኛዎች ጤናማ የሚባል መሆኑንም ነው አስረድተዋል።
ይሁንና አንዳንድ ባንኮች የጥሬ ገንዘብ አጥረት የሚፈጥሩት በራሳቸው የአሰራር ክፍተት መሆኑንና ባንኩ ይህን ለማስተካከል የእርምት እርምጃ እየወሰደ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ፣ ባንኩ በተለያዩ ዘርፎች ያከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች የኢኮኖሚ መረጋጋት እንዲፈጠር ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ አዋጆችን በማሻሻል በተለያዩ ዘርፎች ያከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች የተመዘገበባቸው መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው በጠንካራ ጎን መውሰዱን አንስተዋል።
በተለይም የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል ለመንግስት የሚሰጠውን ብድር ማስቀረት መቻሉ ትልቅ ውጤት አምጥቷል ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ እና መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችቱ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቡ የሪፍርሙ ውጤት ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ባንኩ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ተግባራዊ ያደረገውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።
የውጭ ባንኮችን ሥራ ማስጀመር የሚያስችል መመሪያ መውጣቱን ተከትሎ የሀገር ውስጥ ባንኮች ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን የድጋፍ አማራጮች መፈለግ እንደሚገባም ነው የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው ያመለከቱት።