በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ቁልፍ ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ቁልፍ ተግባር ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2017(ኢዜአ)፦ በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ቁልፍ ተግባር ነው ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) ገለፁ።
13ኛው የግብርና ኤክስቴንሽን ልማት አጋርነት ፎረም የዘርፉ ተዋንያን በተገኙበት ተካሂዷል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ምርትና ምርታማነትን እና ለወጪ ንግድ የሚሆኑ ምርቶችን በመጠንና በዓይነት የሚያሳድጉ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ ገልጸዋል።
የምግብና የስርዓተ ምግብን ዋስትና ለማረጋገጥ ከምርምር ጀምሮ በየደረጃው መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ በግብርና እሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚሳተፉ የዘርፉ ተዋንያን በትብብር መስራት እንደሚገባቸውም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አማካሪ ጭምዶ አንጫላ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በትብብር በተሰራው ስራ በግብርናው ዘርፍ የነበሩ ማነቆዎች እየተፈቱ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁን በግብርናው ዘርፍ ያሉትን ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ወደ መሬት በማውረድ ለተግባራዊነቱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አሸናፊ ክንፈ እንዳሉት፤ የዚህ ዓይነት መድረኮች ያሉትን ደንቦች እና ፖሊሲዎች ለማሻሻልና ስትራቴጂዎችን ለመቅረጽ ሚናቸው ከፍተኛ ነው።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የግብርና ቢሮ ሃላፊ እያሱ አብርሃ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዘርፉ የሚዘጋጁ መድረኮች በተለይ የተሻሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በገበያም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል፡፡