ውበትና ትጋት በህንድ

 በቤተልሄም ባህሩ (ኢዜአ)

በልጅነቴ እያየሁ ያደግኳቸው አብዛኛዎቹ ፊልሞች የህንድ ናቸው። ይህ ደግሞ ከአገራችን አርቲስቶች በላይ የህንድ የፊልም ተዋንያኑን ስም ለመለየት አስችሎኛል። የህፃንነት ዘመኔን የሚያስታውሱኝን ፊልሞች ከትዝታ ማህደሬ እያወጣሁ ከመተረክ በስተቀር ህንድን የማይበት አጋጣሚ ይኖራል ብዬ አስቤ አላውቅም። 

እነዚያን በህንድ ፊልም የማደንቃቸውን የምደመምባቸውን የህንዳውያንን ሶስት ከተሞች ለመጎብኘት ከተመረጡ ከሰሜንና ምስራቅ አፍሪካ የተውጣጡ ጋዜጠኞች መካከል መሆን ድንገቴ ሆነብኝ። እኔም ብቻ ሳይሆን አብዛኛዎቹ የጋዜጠኞች ልዑካን ህንድ ከልጅነት ትዝታቸው ጋር የተሳሰረ አንዳች ነገር አለው። ህንድ በፊልሞቿ የሚያቋት ስለመሆኑ ጉብኝቱን ተከትሎ በተካሄደው በዶርሻን የቴሌቪዥን ጣቢያ ውይይት ላይ ሲያነሱ ሰምቻለሁ። 

በዓለም ላይ በህዝብ ብዛቷ ቀዳሚዋ ህንድ የብዝሃ ባህል፣ ቋንቋና ሃይማኖት አገር ናት። በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኪነ ጥበብ ስራዎቿ በዓለም ላይ ትታወቃለች። ለጉብኝት ከተጋበዙት የጋዜጠኞች ቡድን መካከል አባል ሆኜ በዴልሂ፣ አግራና ባንጋሎሩ ከተሞች በተጓዝንባቸው ስፍራዎች ሁሉ የታዘብኩት ህንዳዊያን በስራና ትጋት ላይ መሆናቸውን ነው። ሁሉም ነገውን ለማሳመር የራሱን ድርሻ ለማኖር፤ ለሀገሩ እድገትና ልማት አሻራውን ለማኖር እንደሚታትር መረዳት ይቻላል።


 

ባረፍንበት ሆቴል ያሉ ሰራተኞች፣ በገበያ ስፍራ የምናገኛቸው ሰዎች እንዲሁም በጎበኘናቸው ስፍራዎች ያሉ ሰዎች  ሁሉ ለሀገራቸው እድገትና ልማት ብሎም ነጋቸውን ለማሳመር የራሳቸውን ድርሻ ለማኖር ይታትራሉ። አብሬ ከነበርኳቸው ጋዜጠኞች ጋር ስናወጋ የምናነሳው በከተማዋ በተጓዝንባቸው ጎዳናዎች የምናየው የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በየተቋማት የሚታትሩ ሰራተኞች እንዲሁም በንግድ የተሰማሩ ሰዎች ደፋ ቀና ማለት ለአገር የሚያደርጉትን ልፋት ነው። 

አንድ ቀን በጋራ ሆነን ወደገበያ ስፍራ ስናቀና በፍጥነት የሚደርሱ ምግቦች ተመግበው ለመሄድ የሚፋጠኑ ህንዳውያንን  ያየ የጋዜጠኛ ቡድኑ አባል መሰል ልምድና ጊዜ አጠቃቀም በአፍሪካም ሊለመድ የሚገባውና የአህጉራችንን የስራ ባህልና እድገት የሚያረጋግጥ መሆኑን የገለጸበት ሁኔታ ለአገሬው ህዝብ ታታሪነት እንደማሳያ አድርጌ ላነሳው ወደድኩ። በሄድንባቸው አካባቢዎች ሁሉ አዲስ ሰው ሲያዩ ለማገዝ አና ስለነገሮች ለማስረዳት የሚፈጥኑ ዜጎችን ተመልክቻለሁ። በተጓዝኩባቸው ከተማዎች ያየኋቸውን ስፍራዎች ከማስታወሻዬ እየነቀስኩ ለእናንተ ላካፍል ወደድኩ። 

በቅድሚያ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የስድስት ሰዓት ተኩል በረራ በማድረግ የመጀመሪያ መዳረሻ ያደረግናትን ዴልሂን እንቃኛለን።

 ዴልሂ- ታሪካዊ ህንፃዎችን ከአዲሶቹ ጋር አጣምራ የያዘች ጥንታዊ ስልጣኔን ከዘመናዊው ጋር አዋህዳ የምታንፀባርቅ ከተማ ናት። በከተማዋ በተዘዋወርንባቸው ስፍራዎች ሁሉ ከጎዳናዎቿ እስከ ህንፃዎቿ ምድረ ግቢ ድረስ በእፅዋት የተሞላችና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትኩረት የሰጠች መሆኗን በግልፅ ያሳየች ከተማ ናት። በዴልሂ ብቻም ሳይሆን በተዘዋወርንባቸው በሶስቱም ከተሞች ጎዳና ስንጓዝ ያየናቸው ግዙፍ ዛፎች ትናንት አገሪቷ ለእፅዋት የሰጠችው ትኩረት ዛሬ ላይ ፍሬ አፍርቶ አስተዋልኩ። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት ዓመታት እየተከናወነ ያለው ተግባር እንዲሁም በኮሪደር ልማት ከተሞችን ፅዱና አረንጓዴ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት አሁን ላይ ካመጡት ለውጥ ባለፈ ለወደፊት የሚኖራቸውንም መዳረሻ አሻግሬ ለማየት አስችሎኛል።  

አሰላሳዮቹ - በዴልሂ ቆይታችን በመጀመሪያ ያቀናነው ጥናቶችን በመስራትና ውይይቶችን በማድረግ በኩል አበርክቶ እያደረገ ያለውን ኦብዘርቨር ሪሰርች ፋውንዴሽን የተሰኘ አሰላሳይና ሃሳብ አመንጪዎች ቡድን (ቲንክ ታንክ ግሩፕ) ነው። ተቋሙ በአገር ውስጥ ባሉ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የመስራት ተልዕኮን አንግቦ የተነሳ ቢሆንም አሁን ላይ ከኢኮኖሚና እድገት ባለፈ በኢነርጂ፣ አካባቢ፣ በደህንነትና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑና ለውሳኔ የሚጠቅሙ ሃሳቦችን በማመንጨት የአገሪቷን ህዝብና መንግስት እያገዘ ይገኛል። ከተቋሙ አባላት ጋር ባደረግነው ቆይታ ለራስ ችግር የራስ መፍትሄ ማምጣት ተገቢ ስለመሆኑ በአጽንኦት አንስተዋል። የአፍሪካ አገራት ትብብር የአህጉሪቷን ልዕልና ለማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑም ተነስቷል። 

የአሰላሳይና ሃሳብ አመንጪዎች ቡድን አባላቱ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ጨርሰን በቀጣይ ያመራነው በህንድ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ባሉ አገራት ጭምር በባቡር መንገድ መሰረተ ልማት ላይ አሻራ እያኖረ ወዳለው ራይትስ ወደተሰኘው ተቋም ነው። የህንድ የባቡር መንገድ የቴክኒካልና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት (Rail India Technical and Economic Service) የተሰኘው ይህ ተቋም ላለፉት 51 ዓመታት በባቡር መንገድ ጠበብቶች አማካኝነት በህንድና በመላው ዓለም ባሉ 62 አገራት በዘርፉ ሲሰራ ቆይቷል።


 

የእጅ ጥበብ ገበያ - ቀጣይ መዳረሻችን ደግሞ ዲል ሃት ኢና የተሰኘው የባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች እንዲሁም የቤት ማስዋቢያዎች መገኛ ወደ ሆነው ገበያ ነው። ገበያው ባይገበዩበትም ዞረው እንዲቃኙ የሚያስገድድ አንዳች ድምቀትን የተላበሰ መሆኑን ባደረኩት ቆይታ አስተውያለሁ። 

የንግድ ማህበር የሆነው የህንድ ኢንዱስትሪ ኮንፌዴሬሽን (ሲአይ አይ) በዴልሂ ቆይታችን ካየናቸው ተቋማት መካከል የሚጠቀስ ነው። ተቋሙ የንግድ፣ ፖለቲካ፣ የትምህርትና የሲቪል ማህበረሰብ አመራር አባላትን በጋራ በማሰለፍ ዓለም አቀፍና የኢንዱስትሪ አጀንዳዎችን እንዲቀርፁ የሚሰራ ነው። 

አደጋን የሚቋቋም መሰረተ ልማት ጥምረት (CDRI) በነበረን ቆይታ ጥምረቱ ከአገራት፣ ከተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎችና መርሃግብሮች፣ ከፋይናንስና የግል ተቋማት ጋር በመተባበር የአየር ንብረትና የአደጋ ስጋትን የሚቋቋም መሰረተ ልማት አስተዳደር ላይ እየሰራ መሆኑን ተገንዝበናል። ጥምረቱ የአደጋ ምላሽና መልሶ ማቋቋም፣ በተቋማትና ህብረተሰብ አቅም ግንባታ ድጋፍ ላይ ይሰራል። ጥምረቱ 46 አባል አገራትና ስምንት አጋር ድርጅቶች ያሉበት ሲሆን፤ አገራትና ዓለም አቀፍ አካላትን በማስተባበር የገንዘብና ቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርግ የጥናትና ፈጠራዎች ውጤቶች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን የሚጋሩበትም ነው።


 

የህንድ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዴልሂ(IIT Delhi) ሌላው የጉብኝት መዳረሻችን ነበር። ኢንስቲትዩቱ በኢንጂነሪንግና ሳይንስ ጨምሮ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በርካታ ሰዎችን አስተምሮ ያስመረቀ ሲሆን፤ የተለያዩ ሳይንቲስቶች፣ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችና ስራ ፈጣሪዎችን ማፍራት የቻለ ተቋም መሆኑን መገንዘብ ችለናል።

ብሄራዊ ሙዝየም - በኒው ዴልሂ የሚገኘው የህንድ ብሄራዊ ሙዚየም በአገሪቱ ያለ ትልቁ ሙዚየም ሲሆን፤ በጉብኝታችን ወቅት ለዘመናት የቆየች ቅሪተ አካልን ጨምሮ፣ የተለያዩ የጥበብ ውጤቶችና የታሪክ አሻራ ማሳያ ስራዎችን ቀርበው ይጎበኙበታል።

በዴልሂ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተደረገልን የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባባልና ውይይት ህንድና አፍሪካ የጠነከረ ቁርኝት ያላቸውና በንግድ አጋርነትት  በቀዳሚነት የሚጠቀሱ መሆኑ ተመላክቷል። በተደረገልን ገለፃ  ህንድና የአፍሪካ የንግድ መጠን 100 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ነው። 


 

ህንድ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፣ ፋርማሲዩቲካል ፣ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪዎች ፣ ማዕድን እና የባንክ ዘርፎችን ያላት የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ወደ 75 ቢሊዮን ዶላር ገደማ መድረሱም ተገልጿል። ኢትዮጵያም ከህንድ ጋር ለዘመናት የዘለቀ ወዳጅነት ያላትና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷም ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑ ተነስቷል። ሁለቱ አገራት ያላቸው ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ ብቻ ሳይሆን በባህል ትስስር ጭምርም የተጋመደ መሆኑ ተመላክቷል።  ለወደፊቱም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአህጉሪቱ ካሉ አገራት ጋር የምታደርገው ትብብርና ወዳጅነት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑም ተነስቷል።  

አግራ- የህንድ ታሪክ፣ ባህልና ኪነ ህንፃ መገለጫ በሆነችው አግራ ተገኝተን የጎበኘነው ህንድ ስትነሳ ስሙ ተያይዞ የሚነሳውን ታጅ መሃልን ነው። ታጅ መሃል በእምነ በረድ የተሰራ ውብ ኪነ ህንፃ ሲሆን፤ ንጉስ ሻህ ጃሃን ከሌሎች ሚስቶቹ ሁሉ አስበልጦ ለሚወዳት ሚስቱ ሙምታዝ መሀል ክብር ሲል የገነባው ድንቅ የእጅ ስራ ውጤት ነው። ታጅ መሃልን ስንጎበኝ የነበረው ሙቀት ሀይለኛ ቢሆንም ላባችን እየተንቆረቆረ ንጉሱ ለፋርስ ልዕልቷ ሚስቱ የነበረውን ፍቅር በተመለከተ በአስጎብኚያችን የሚሰጠንን ማብራሪያ ስናደምጥና የፍቅር ሃያልነትን ስናደንቅ ነበር።   

በዴልሂ ከጉብኝታችን ባሻገር በኢንዲያን ጌትና በገበያ ቦታዎች እንዲሁም በከተማዋ ጎዳናዎች ተዘዋውረን የህዝቡን ፍቅርና ተባባሪነት አይተናል። በተለይ ቦታ የጠፋን መሄድ ያሰብንበት ቦታ እንዳለ የሚያመላክት ፍንጭ በግርታችን ያስተዋሉ ከመሰላቸው "እዚህ መሄድ ፈልገህ ነው ይህን እዚህ ማግኘት ትችላለህ" የሚል ጥቁምታ በመስጠት እንግዳ ተቀባይነትና ሰው አክባሪነታቸውን ይገልፁልሃል። 

በዴልሂና አግራ የነበረንን ጉብኝትና ትዝታ እያሰላሰልን ቀጣይ መዳረሻ ያደረግናት ባንጋሎሩ ከተማን ነው።  ባንጋሎሩ ቀጣይ ትረካችን ይሆናል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም