በ“ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ” ንቅናቄ የተመዘገቡ ውጤቶችን ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በ“ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ” ንቅናቄ የተመዘገቡ ውጤቶችን ማጠናከር ይገባል
ሀዋሳ፤ ሰኔ 20/2017 (ኢዜአ) ጽዱ እና ለኑሮ ምቹ አካባቢን ለመፍጠር በተጀመረው “ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ” ንቅናቄ የተመዘገቡ ውጤቶችን ማጠናከር እንደሚገባ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ።
በሲዳማ ክልል “ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ” በሚል ሀሳብ ለቀጣይ ስድስት ወራት የሚተገበር ሁለተኛው ክልል አቀፍ የህዝብ ንቅናቄ መርሃ ግብር በሀዋሳ ፍቅር ሀይቅ ዳርቻን በማጽዳት በይፋ ተጀምሯል።
መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ባለፉት ጊዜያት ጽዱና ምቹ አካባቢን ለመፍጠር በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ በተከናወኑ ስራዎች ውጤት መምጣቱን ተናግረዋል።
በተለይም የህዝብን የግንዛቤ ስራዎች በማሳደግ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
የተመቸና ጽዱ አካባቢን ለመፍጠር የተጀመረውን ንቅናቄ ለማጠናከር ተግባሩን በተደራጀ መልኩ በማስቀጠል ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል ።
በመርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴራል የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው እንደ ሀገር ባለፉት ስድስት ወራት “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው ንቅናቄ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
በዚህ ንቅናቄ የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል “ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ” በሚል መሪ ሃሳብ በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት በሚቆየው ንቅናቄ ከ15 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የአካባቢ ብክለትን መከላከልና የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች እንደሚተገበሩም ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል ደን አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽታዬ ዩሙራ በበኩላቸው በክልሉ በንቅናቄው የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ህብረተሰቡ ጽዳትን ባህል እንዲያደርግ ግንዛቤን ለማሳደግ በተከናወነው ስራ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው ይህንንም ለማጠናከር በሚያስችል መልኩ ወደ ስራ መገባቱን አስረድተዋል።
በዘመቻው የተሳተፉት የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ዱጉና ዱካሞ ጽዳትን ባህል ማድረግ ጤናን ለመጠበቅና ለኑሮ የተመቸ አካባቢን ከመፍጠር አንጻር ጥቅሙ ብዙ በመሆኑ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የሲዳማ ክልልና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።