የስፖርት ዘርፉን ለማሳደግ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማልማት ሥራ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት ዘርፉን ለማሳደግ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማልማት ሥራ ይጠናከራል

ሀዋሳ፤ ሰኔ 20/2017 (ኢዜአ )በሲዳማ ክልል የስፖርት ዘርፉን ለማሳደግ የስፖርት የማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማልማት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለፁ።
የክልሉ መንግስት ለሲዳማ ቡና እግር ኳስ ቡድን ያዘጋጀው የማበረታቻ ሽልማትና የዕውቅና መርሃ ግብር በሀዋሳ ከተማ ተካሄዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስዳድር ለቡድኑ 19 ሚሊዮን ብር እና ሌሎች ሽልማቶችን ያበረከቱ ሲሆን የቡድኑ አባላትም ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እጅ የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተረክበዋል።
የ2017 የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ዋናው ቡድን ለ17 ተጫዋቾች ለእያንዳንዳቸው 200 ካሬ ሜትር የቤት መስሪያ ቦታና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ለሆነው የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ቡድን አባላትም የ4 ሚሊዮን ብር የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በተመሳሳይም በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 3ኛ ደረጃን ይዞ ላጠናቀቀው የሲዳማ ቡና ሴቶች እግር ኳስ ቡድንም የ4 ሚሊዮን ብር ሽልማት ተበርክቷል።
በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር 5ኛ ደረጃን ይዞ ላጠናቀቀው የሀዋሳ ከነማ እግር ኳስ ቡድን የ3 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለሲዳማ ቡና እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ማህበር የ1 ሚሊዮን ብር ሽልማት ተሰጥቷል።
ሽልማቱን ተከትሎ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ቡድኑ ባስመዘገበው ውጤት የክልሉ ህዝብና መንግስት ደስታ እንደተሰማው ገልፀዋል።
የተገኘው ውጤት እንዲጠናከርም የክልሉ መንግስት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመው ዘርፉን የመደገፍና በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የስፖርት የማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማልማት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ እና የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።